የሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጋር በማቀናጀት ኢኮኖሚውን ለማጠናከር በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገለጸ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን (STI) መር ዘላቂና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ማቀናጀትና ማዘመን ላይ ያተኮረ ለዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ በሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች እና በሳይንስና የቴክኖሎጂ መረጃዎች ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ቀደም ሲል ለባለሙያዎች የተሰጠውን የአሰልጣኞች ስልጠና (😭) ተከትሎ፣ በክልሎች የሚሰጠው ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በጋራ ለመምራትና የአመራሩን የቴክኖሎጂ ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተክለማሪያም ተሰማ ከሀገር በቀል እውቀት ጋር በማጣመር በቅንጅት መስራት የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘርፉ አመራሮች የቴክኖሎጂን ፋይዳ ለይተው በማወቅና ለተገልጋዩ ማህበረሰብ በማስረዳት ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለባቸው ዶ/ር ተክለማርያም በአጽንኦት አሳስበዋል። የሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንሳዊ ምርምር ግኝቶች ጋር በማጣመር የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው በቁርጠኝነት እየተተገበሩ ይገኛሉ ብለዋል። ኢትዮጵያ በሳይንስ መር ኢኮኖሚ ግንባታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የኢንዱስትሪ ችግሮችን የሚፈታና እውቀት ላይ የተመሰረተ የሰው ሀይል ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በክልል ቢሮዎች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ለተግባራዊ ስራዎች ጠንካራ መሰረት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል። በመጨረሻም በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ አስተዳደር፣ በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በቀረቡ ጽሁፎች ላይ ሰፊ ምክክር ከተደረገ በኋላ የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።