Skip to main content

message

የቢሮው ሀላፊ መልዕክት

ሳይንስና ኢንፎርመሽን ቴክኖሎጂ   ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የሚያበረክተው  አስተዋጽኦ ከምንም በላይ መሆኑን ዛሬ ላይ የስልጣኔ ጫፍ የደረሱ፣ የበለፀጉና የዓለማችን ሃያላን ተብለው የሚጠሩ አገሮች ምሥክሮች ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ መንግስት የሀገራችን ሕዝብ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆንና የቴክኖሎጂው ሽግግር ከጫፍ እንዲደርስ ተግቶ በመሥራቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀላል የማይባል የሀገራችን ሕዝብ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡  ለዚህም ማሳያ መሆን የሚችሉ በርካታ ተግባራትን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በክልላችን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከሚመለከታቸው /ቤቶች ጋር በመሆን በአያሌ የገጠር ቀበሌያትና ወረዳዎች የገጠሩ ሕብረተሰብ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሌሎች የመረጃ ምንጮች የሚፈልጓቸውን መረጃዎች በተለያዩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች አማካይነት ማግኘት እንዲችሉ የማህበረሰብ መረጃ ማዕከላትን አቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡  ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሽቦ አልባ ስልኮችም በብዙ የገጠር ቀበሌያት በቢሮውና አግባብነት ባላቸው ተቋማት በኩል የተሠራጩ ሲሆን እስኩል ኔትና ወረዳ ኔቶችም እንዲሁ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በክልል ማዕከል፣ በዞኖች፤ በልዩ ወረዳዎች፤ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  መሠረተ ልማት ደረጃ በደረጃ እየተዘረጋ ያለ ሲሆን በዋናነት የመንግስት መረጃ ሥርዓት  የማሳለጥ፣ የቪዲዮ ኮንፍረንስ አገልግሎት በመስጠት ፈጣን የሆነ መረጃ እንዲዳረስ የማድረግና የማህበረሰብ መረጃና ሬድዮ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን ወደ ስራ እያስገባ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢኮቴ ዘርፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተመራቂዎችን በማህበር በማደራጀት የተለያዩ ድጋፎችን ማለትም ስልጠና፣ የገበያ ማፈላለግና የማማከር አገልግሎት በመስጠት የግል ካምፓኒ ፈጥረው  ወደ ንግድ ዓለም እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቢሮውን ዌብ ሳይት በማልማት እና የፌስቡክ ገጽ በመክፈት እንዲሁም የተለያዩ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተቋማችን አጠቃላይ አፈጻጸምና ሁኔታ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እተከናወነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ቢሮው ከክልል እስከ ወረዳ/ከተማ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት፣ ከማስፋፋትና ክህሎትን ከማዳበር አንፃር ያከናወናቸው አበረታች ተግባራት ቀጣይነት  እንዲኖራቸው ባለድርሻ አካላት ዘርፉ በክልላችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲበለጽግና ሕዝባዊ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡

ከሳይንስና ፈጣራ ስርጸት አንጻር በየአከባቢው ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማበረታታት የዜጎች የመገናኘት ሁኔታ በማሳለጥ ምርታማነትንና ተጠቃሚነትን ለመጨመር የሚያስችል ተግባር በመፈጸም ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ግብ ለማሳካት ርብርብ የሚደረግ ይሆናል፡፡

 ስለዚህ በክልላችን የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ት/ቤቶች፣ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች በሙሉ ሀገራችን አድገ  ወደ ታቀደው ስፍራ ለመድረስ የሳይንስና ኢንፎርመሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተገንዝበው ጥያቄዎችን በራስ ተነሳሽነት ጭምር በማቅረብ እና ከቢሮው ጋር በቅርበት በመስራት የታቀደው ግብ ላይ ለመድረስ ሁላችንም የበኩላችንን እንድንወጣ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ፡፡

አቶ ሰላሙ አመዶ ዋጨንጎ

ሳይንስና ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ቢሮ  ኃላፊ