Admin2
Wed, 12/25/2024 - 15:45

የኮዲንግ ሥልጠና ሂደትን በጉራጌ ዞን አበረታች ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። (ሆሳዕና፣ ታህሳስ 16/2017) ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጰያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ አገና ከተማ አስተዳደር የኮዲንግ ሥልጠና ሂደትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ቢሮ ኃላፊው የኮዲንግ ሥልጠና ሂደት በጉራጌ ዞን አበረታች ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠናውን ሂደት ምልከታ ባደረጉበት ወቅት ነው። በዌብ-ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች የኮዲንግ መሠረታዊ ክህሎት ሰልጣኞችን ነው አቶ ሰላሙ ተዘዋውረው የተመለከቱት። ቢሮ ኃላፊው አቶ ሰላሙ ስለስልጠናው አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ለሰልጣኞች ማብራሪያ ሰጥተው፤ ሰልጣኞችን አበረታተዋል። በእዣ ወረዳ እስካሁን በተለያየ ደረጃ 560 ሰልጣኞች ስልጠና አጠናቀው ሰርተፊኬት ማግኘታቸው ከወረዳው የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ተማሪ ቤዛዊት ፍሬዘር እና ወጣት ጌታቸው ሽርጋ በአራቱም ዘርፍ ስልጠናውን ተከታትለው መጨረሳቸውን እና ሰርተፍኬት ማግኘታቸውን ተናግረው፤ ባገኙት ስልጠና ብዙ መስራትና ተጠቃሚ መሆን እንዳሰቡ ገልጸዋል። የኮዲንግ ሥልጠና ሂደት ምልከታ በወልቂጤ ከተማም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።