Skip to main content
zena7

ተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በብቃት እንዲጠቀሙ የሚያስችል አቅም ለመገንባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ። ቢሮዉ ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ ባለሙያዎች በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ጥገናና እድሳት ላይ ያዘጋጀው የተግባር አቅም ግንባታ ስልጠና በወራቤ ከተማ እየተሰጠ ነዉ። ስልጠናውን ያስጀመሩት የቢሮው ምክትልና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንደተናገሩት በክልሉ የመንግስት ተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በብቃት እንዲጠቀሙ የሚያስችል አቅም ለመገንባት ቢሮዉ በትኩረት እየሰራ ነዉ። የስልጠናው አላማ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ የሚያስችል የአጠቃቀም ግንዛቤና ክህሎት አቅም ማጎልበት መሆኑን አቶ ከበደ ጠቁመዋል። ስልጠናዉ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ሲበላሹ ባለሙያዎች በቀላል ወጪና ግብዓት ጠግነውና አድሰው ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ዕውቀት እንዲያገኙ ታስቦ መዘጋጀቱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። እንደአቶ ከበደ ገለጻ ተረፈ-ጥገና ቁሳቁሶች አካባቢን ሳይበክሉ ወደተመረቱበት ሀገር ሰብስቦ የመላክ ስራ ከስልጠናው በሚገኝ ግንዛቤ በጉልህ ይጠናከራል ተብሎ ይጠበቃል። በየተቋማቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግዥ ሲፈጸም ለታለመለት አገልግሎት ተመጣጣኝና ተገቢ መሳሪያ እንዲገዛና ብክነት እንዲቀንስ ስልጠናው ምክረ-ሀሳብ የመስጠት አቅም ያጎለብታል ሲሉም አቶ ከበደ አክለዋል። ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና የኮምፒዩተር፣ የፎቶ ኮፒ ፣ የፕርንተር፣ የስካነርና የፋክስ ማሽን ጥገናና እድሳት ስልጠና በጽንሰ-ሀሳብና በተግባር ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል