
ህዳር 6/2017 ዓ.ም በሳይንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ውጤታማ ስራ በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ከኢንተርፕሪነር ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ለዞን፣ ለልዩ ወረዳ አመራሮችና ለባለድርሻ አካላት ለተከታታይ 3 ቀናት በወልቂጤ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራና ስርፀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሁዲን ሁሴን እንዳሉት የስልጠናው አላማ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅም በማሳደግ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው። ስልጠናው በሀገር ደረጃ ከኢንተርፕሪነር ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በፐብሊክ ኢንተርፕሪነር እና በኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ለሶስት ተከታታይ ቀናት መስጠቱን አመልክተዋል። ሰልጣኞች የወሰዱትን ስልጠና በተገቢው በመጠቀም ፐብሊክ ኢንተርፕሪነር በመሆን የኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ማስተካከል፣ መደገፍና የተሻለ የፈጠራ ስራ በመስራት ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ስራዎችን የሚደግፉ ስራዎችን በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። እንደ ሀገር ብሎም ክልል መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት እንደሚገኝ ያነሱት ኃላፊው በክልሉ በአንዳንድ መዋቅሮች የሰው ሀይል እጥረትና የበጀት እጥረት መኖሩን ተከትሎ ይህም በቀጣይ በቅንጅት መፍታት ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በክልሉ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ያነሱት አቶ ሙሁዲን ለዚህም በክልሉ በሁሉም መዋቅር የፈጠራ አቅምና ሀሳብ ያላቸው ልጆች መኖራቸውን አንስተው ስልጠናውም ይህንን ወደ ፈጠራና ቴክኖሎጂ የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ሀገር በሳይንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር የማሳደግ፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን የማሻሻል፣ የመተግበርና የመፈጸም፣ የፈጠራ ባህል የማጎልበትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በትኩረት አጠናክሮ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል። አሰልጣኝ አቶ ካሳ አምባዬና አሰልጣኝ ሰላማዊት አሰግድ ስልጠናው በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ስልጠናው በፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕና ኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ግንባታ ላይ መስጠታቸውን አንስተው ይህም ወቅቱና ዘመኑን የዋጀ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል። ሰልጣኞች በስልጠናው ወቅት ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ወደ አካባቢያቸው በመውሰድ ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። አቶ ደምስ ገብሬ፣ አቶ አምባዬ አበራንና ወይዘሮ ገነት ሙሉጌታ በስልጠናው ወቅት አግኝተን ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች በጋራ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ወቅታዊና በተቋም አሰራር ላይ የነበረባቸውን ክፍተት እንደሞላላቸው ተናግረዋል። ሰልጣኞች ያገኙትን ስልጠና በተገቢው በመጠቀም በዘርፉ ውጤታማ ስራ በመስራት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚተጉ አንስተዋል። እንዲሁም በሳይንስ ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በሆኑት በአቶ አምደወርቅ ዘመዱ ቴክኖሎጂን እንደምርት በሚል ርዕስ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም እንደመዋቅር አሁናዊ ሁኔታ የሚገልጽ አጠቃላይ ሁኔታ በማቅረብ ግምገማ ነክ ስልጠና በማድረግ ሁሉም መዋቅሮች በቀጣይ ጊዜያት ለተሻለ አፈጻጸም እንደሚሰሩ መግባባት ተችሏል፡፡ በመጨረሻም ለሰልጣኞች የማበረታቻ ሽልማትና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።