
ህዳር 4/2017 ዓ.ም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢንተርፕሪነር ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ለዞንና ለልዩ ወረዳ አመራሮችና ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በወልቂጤ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል። ስልጠናው በፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና ኢኖቬሽን ኢኮሲስተምና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ድጋፍ አሰጣጥና አስተዳደር ዙሪያ ለ3 ተከታታይ ቀናት በመስጠት ላይ ነው። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራና ስርፀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሁዲን ሁሴን በመክፈቻ ንግግራቸው ቢሮው ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሳይንስ ኢንቬሽን ቴክኖሎጂ ስራዎችን በተገቢው በማልማት፣ በመተግበር፣ በማስፋፋትና ክልላዊ ብሎም ሀገራዊ ተወዳዳሪነት አቅም በቴክኖሎጂ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው የተከማቸና አቅም የሆነ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መፍጠር ሲቻል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙህዲን ለዚህም ቴክኖሎጂ የመረዳት፣ የመጠቀም፣ የመፍጠር አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል። ቴክኖሎጂን በተሻሻለ አቅም ጥራት በማምረትና በመጠቀም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ዘርፍ ተጽኖ ለመፍጠር የተጀማመሩ ጅምር ስራዎችን ማጠናከር ሲቻል በመሆኑ ለዚህም በክልሉ በዘርፉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በሳይንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር የማሳደግ፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን የማሻሻል፣ የመተግበርና የመፈጸም፣ የፈጠራ ባህል የማጎልበትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በትኩረት አጠናክሮ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል። በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚቻለው ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንቬሽን ስራዎችን በውጤታማነት ሰርቶ ማሸጋገር ሲቻል መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ለዚህም የተጀማመሩ ስራዎችን ወደ ውጤት ለመቀየር የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል። ስልጠናው የሳይንስ ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።