
ኢትዮ ኮደርስ በክልሉ በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናገሩ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ የሀገሪቱን ዲጂታል ክህሎት ከፍ ለማድረግ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዲጂታል ኮደርስ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ አንተነህ ይህን የተናገሩት የዋን- ዋሽ፣ የኮ-ዋሽ ፕሮግራም አፈፃፀም ለመገምገም፣ የፕሮግራሙ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የኢትዮ ኮደርስ ላይ ለመወያየት በወልቂጤ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ነው። የኢትዮ ኮደርስ የኢፌዴሪ ጠቅይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬት መንግስት ጋር በመሆን በተገኘ ድጋፍ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አንተነህ ስልጠናው በነፃ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ ሀገር 5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሰለጥኑ መታቀዱን ያነሱት አቶ አንተነህ በክልሉ በየመዋቅሩ ስልጠናው መጀመሩን ገልፀው በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ዜጎች ስልጠናውን በመውሰድ የዲጂታል ክህሎታቸውን ከፍ በማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በክልሉ በሚሰጠው ሀገር አቀፍ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ላይ በመሳተፍ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑም አቶ አንተነህ ጥሪ አቅርበዋል።