ክልሉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ የባለሞያዎች ቴክኒካል ክህሎት ማሳደግ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ። (ወራቤ፣ ሚያዝያ 21 /2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ባለሞያዎች በሆሳዕና ከተማ ሲሰጥ የቆየው 2ኛ ዙር ቴክኒካል ስልጠና ተጠናቀቀ።
የቢሮው ምክትልና የዲጅታላይዜሽን ዘርፍ ሀላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ በማጠቃለያው እንደገለፁት ክልሉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ የባለሞያዎች አቅም በቴክኒከል ክህሎት መገንባት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ማህበረሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ከበደ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቶች የኦንላይን ስራ እንዲያገኙ በማድረግ ውጤት እየመጣ መሆኑን አስታውቀዋል። ሲስተሞችን በማልማት ቀልጣፋ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዌብ መተግበሪያ የሚለቀቁ መሠረተ ልማቶችና መረጃዎችን ደህንነት በማስጠበቅ የዲጂታል አገልግሎት ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ወጣቶች አለም አቀፍ ስልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ የሰው ሀይልን በቴክኒካል ክህሎት የማሳደግ ስራም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ስልጠናው በ2ኛ ዙር (Web Application security, Cloud Computing and IT Project Management) ላይ ሲሆን አቶ ከበደ የለሙ ዌብ መተግበሪያዎች ከጥቃት በመከላከል እንዴት መጠቀም እንደሚገባ እና ጥቃቶችን እንዴት መከላከል እንደሚቻል አቅም ይፈጥራል ብለዋል። የሀገር ደህንነት የሚጠበቀው የሳይቨር ሴኩሪቲ ደህንነት ሲጠበቅ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት ዜጎች እንዲያገኙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማብቃት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ እየረቀቀ የመጣበት ጊዜ በመሆኑ የለሙ መሠረተ ልማቶችና መረጃዎች በክላውድ(Cloud) ላይ መገንባትና መጠቀም የሚስችል አቅምን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል። የአይቲ መሠረተ ልማቶች በአይቲ ክህሎት መምራትና ማስተዳደር የሚያስችል እውቀት በመቅሰም ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል። በክልሉ የቴክኖሎጂ ምርቶች ውጤት አዳጊ እንዲሆን እንዲሁም ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የስልጠናው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆን አቶ ከበደ ተናግረዋል። በስልጠናው ከክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከዞኖች እና ከልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል። የ3ኛ ዙር ስልጠና በሌሎች ኮርሶች በምቀጥለው ቀናት የምጀምር ይሆናል።