Skip to main content
zena97

የክልሉን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያዎች አቅም በዲጅታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የዜጎች አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየተሰራ ነው:-

የክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ (ሆሳዕና፣ ሚያዝያ) 14/2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሶፍትዌሮችን ማበልፀግ የሚያስችል ስልጠና ለዘርፉ ባለሞያዎች እየሰጠ ይገኛል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የዲጅታላይዜሽን ዘርፍ ሀላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ የክልሉን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያዎች አቅም በዲጅታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የዜጎች አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል። ቢሮው የክልሉን ህዝብ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዲጂታል 2030ን እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሶፍትዌሮች ማልማትና የለሙትን በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል አቅም ለመገንባት የባለሞያዎች ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ከበደ አመላክተዋል። ሶፍትዌሮችን እንደ ቁሳቁስ እየገዙ ሟሟላት እንደማይቻል የጠቆሙት ሀላፊው ውስብስብና በግዥ ደረጃም ውድ በመሆናቸው አልምቶ መጠቀም አዋጭ መሆኑን አስታውቀዋል። የዲጅታል አገልግሎት ማስፋፋት የተገልጋይን ጊዜ፣ገንዘብና ጉልበት በመቆጠብ ጥራት ያለው ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በ17 ከተሞች ለማስፋፋት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ከበደ ስልጠናው በራስ አቅም ሶፍትዌሮች በልፅገው በየማዕከሉ ዲጅታል አገልግሎት በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ አቅም ይፈጥራል ብለዋል። ቴክኖሎጂን በተገቢው መጠቀም የሚችል ዲጂታል ማህበረስብ በመፍጠር የዜጎችን እርካታ ከፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ስልጠናው ከክልሉ ሁሉም መዋቅር ለተውጣጡ ባለሞያዎች ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚሰጥ መሆኑን የገለፁልን አቶ ከበደ ለሠልጣኞች ወቅታዊ የሆኑ ሶፍትዌሮች ማበልፀግ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።