Skip to main content
Zena15

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስካሁን 23 ሺህ ገደማ ሰልጣኞች የኮዲንግ ሥልጠና መሰልጠናቸው ተገለጸ። (ሆሳዕና፣ ታህሳስ 16/2017) ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጰያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በጉራጌ ዞን የኮዲንግ ሥልጠና ሂደትን ምልከታ አድርገዋል። የኮዲንግ ሥልጠና በሀገር ደረጃ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚሰለጥኑበት ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ መሆኑን በማስታወስ፤ በክልል ደረጃ በሶስት አመት ውስጥ ከ198 ሺህ በላይ አሰልጣኞችን ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ተናግረዋል። ቢሮ ኃላፊ አክለው እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት አመት በክልሉ 50 ሺህ ሰልጣኞችን የኮዲንግ ስልጠና ለማሰልጠን ታቅዶ እስካሁን 23 ሺህ ገደማ የሚሆኑትን ማሰልጠን ተችሏል። በወልቂጤ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት እንዲሁም በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኮዲንግ ሥልጠና ሂደትን አቶ ሰላሙ ያዩ ሲሆን፤ አበረታች አፈጻጸም መመልከታቸው ተናግረዋል። ሰልጣኞችንም በቦታው አበረታተዋል። በዌብ-ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች የኮዲንግ መሠረታዊ ክህሎት ለማዳበር የሚያስችሉ ነጻ የኦንላይን ሥልጠና እድሎችን መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። ቢሮ ኃላፊው የጉራጌ ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ለኮዲንግ ስልጠና ግብዓት የሚሆኑ ዴስክ ቶፕችንና ላፕቶፖችን በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት የተሰራውን ስራ አድንቀዋል። የዞኑ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው፤ በእዣ ወረዳ አገና ወልቂጤ ከተሞች የኮዲንግ ሥልጠና ሂደት ላይ በክልል ደረጃ ምልከታ መደረጉ እንዳስደሰታቸውና ቀጣይ ለስራ እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል። የኮዲንግ ሥልጠና ሂደት ምልከታ ነገ በዱራሜ ከተማ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።