Skip to main content
Zena14

የኮዲንግ መሠረታዊ ክህሎት ለማዳበር የሚያስችል ነጻ የኦንላይን ሥልጠና እድልን ሁሉም ወጣቶች እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ። (ሆሳዕና፣ ታህሳስ 17/2017) ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻቤቦ በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ የኮዲንግ ሥልጠና ሂደትን ተመልክተዋል። በዞኑ የኮዲንግ ሥልጠና ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን አቶ ከበደ ተናግረው፤ የኮዲንግ መሠረታዊ ክህሎት ለማዳበር የሚያስችል ነጻ የኦንላይን ሥልጠና እድልን ሁሉም ወጣቶች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። የስልጠና ሂደቱን የተመለከቱት በዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና በሂጋ ሞዴል ትምህርት ቤት ሲሆን ለሰልጣኞች ስለ ኮዲንግ ስልጠና አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊው አቶ ከበደ የኦንላይን ስልጠናውን በስምንት ሳምንታት ለሚያጠናቅቁ ብቁ ሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰርተፊኬት የሚበረከትላችሁ መሆኑን አውቃችሁ መበርታት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ የከምባታ ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ አምባዬ አበራ በዞኑ የኮዲንግ ስልጠና ሂደት ላይ በክልል ደረጃ ምልከታ መደረጉ ለቀጣይ ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል። በዞኑ እስካሁን ድረስ ከ2 ሺህ 300 በላይ የኮዲንግ ሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለው፤ በተለያየ ደረጃ ሰርተፊኬ ማግኘታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። ተማሪ መቅደስ ከባሞ በዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሁለተኛ አመት ተማሪ መሆኗን በመግለጽ ለቀጣይ ስራ እንዲረዳት በዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች ስልጠና መከታተል መጀመሯን ተናግራለች። በሂጋ ሞዴል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዳግማዊ ተሾመ በዌብ-ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች ስልጠናው አጠናቆ ሰርተፊኬት መቀበሉን ገልጿል። በሰለጠነባቸው ዘርፎችም ብዙ መስራት እንዳሰበ ተናግሯል።