Skip to main content
zena82

ታህሳስ 25/2018(ወልቂጤ) ‎የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር የተሰራው ዘመናዊ የእንሰት ማዘጋጃ ቴክኖሎጂ ለወጣቶች የማሸጋገርና ማስተዋወቅ መርሀግብር በቸሃ ወረዳ የሰስየ ቀበሌ ተካሄደ። ‎ ‎የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንሰት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የሰብል አይነት ቢሆንም ከተከላው ጀምሮ ለምግብነት እስኪውል ድረስ ከፍተኛ ድካም አለው። በመሆኑም ከፍተኛ ወጪ፣ ጉልበትና ጊዜ የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል። ‎ ‎የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ይህንን ጫና የሚቀንስ፣ ምርትን በጥራት የሚያዘጋጅና ብክነትን የሚቀንስ ዘመናዊ የእንሰት ማዘጋጃ ቴክኖሎጂ በመሰሸጋገሩ ምስጋናቸው አቅርበው ወጣቶች ተደራጅተው ቴክኖሎጂው በመጠቀም ውጤታማ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል። ‎ ‎እንደ አቶ ላጫ ጋሩማ ቴክኖሎጂው ቆጮና ቡላ በጥራት ከማዘጋጀት ባሻገር ብክነትን የሚከላከል በመሆኑ ቴክኖሎጂው በሁሉም አካባቢዎች ማስፋፋት ይገባል ሲሉ ገልፀዋል። ‎ ‎የኢትዮጵያ ባዮና ኢመርጂን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር ካሳሁን በበኩላቸው የእንሰት ሰብል ድርቅ የሚቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚከላከልና ተመራጭ የምግብ ሰብል በመሆኑ በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት የምርምር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው አስረድተዋል። ‎ ‎ሰብሉ ለምግብነት እስኪውል ድረስ የሚወስደው ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቀነስ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲሰራ እንደነበር የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ለሽግግር የበቃው ቴክኖሎጂ ሙሉ ወጪው በመሸፈን አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል። ‎ ‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንሰት በሀገሪቱ በተለይም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስፋት የሚመረት ለምግብነት የሚውል ሰብል ነው። ‎ ‎ይህን እንሰት የክልሉ አርማ በማድረግ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ሀውልት እንዲቆምለት ተደርጓል ብለዋል። ‎ ‎እንደ ኃላፊው ገለፃ እንሰት ጥቅም ላይ ለማዋል ባህላዊ መንገድ በመከተል ይዘጋጅ እንደነበርና ይህ ቴክኖሎጂ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ከመቀነስ በተጨማሪ ምርትን በጥራት ለማዘጋጀትና ብክነት ለመከላከል ያስችላል ብለዋል። ‎ ‎ቴክኖሎጂ ለወጣቶች ማሸጋገር የተቻለ ሲሆን ወጣቶች ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ በመፍጠር ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንሰትን በተገቢው መንገድ ለምግብነት ለማዋል የሚጠይቀው ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተናግረዋል። ‎ ‎ቴክኖሎጂው የእንሰት ውጤቶችን በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያስችላል ብለዋል። ከዚህ ቀደም አንዲት እናት በቀን ሁለት እንሰት ብቻ ትፍቅ የነበረ ሲሆን ቴክኖሎጂው ግን እስከ 40 እንሰት የመፋቅ አቅም አለው። ‎ ‎የቸሃ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አንዳምላክ ይብጌታ እናቶች በባህላዊ መንገድ ይፍቁ ስለነበር በሚፈጠርባቸው የስራ ጫና ለፌስቱላ በሽታ እንዲዳጉ ምክንያት እንደነበር ገልፀዋል። ‎ ‎በመሆኑም ይህ ቴክኖሎጂ የእናቶች ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ የሚቆጥብ የቴክኖሎጂ ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል። ‎በተጨማሪም ወጣቶች ቴክኖሎጂው ተጠቅመው በመስራት ኢኮኖሚያቸው ማሳደግ አለባቸው።