Skip to main content
zena71

ዘመናዊ የመረጃ ማደራጃ ሲስተም ዳታቤዝን ተግባራዊ በማድረግ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ። ጥቅምት 12/2018፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ እና በጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ያስለማውን የመረጃ ማደራጃ ዳታቤዝ ሲስተም ተረክቧባ። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር ለክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ያለሙትን የመረጃ ማደራጃ ሲስተም (ዳታቤዝ) ዛሬ አስረክበዋል። በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትልና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ ራህመቶ፣ ዘመናዊ የመረጃ ማደራጃ ዳታቤዝ ሲስተምን ተግባራዊ በማድረግ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ገልፀዋል። የለማውን ዳታቤዝ ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር በየደረጃው ለሚገኙ ባለሙያዎችና አመራሮች የማስተዋወቅና የተግባቦት መድረክ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል። በሂደቱም የክልሉ ሴቶች ልማት ህብረት ዳታቤዝ በማልማት የአደረጃጀትና የአባላትን መረጃ ከ90 በመቶ በላይ ማደራጀት መቻሉንም ወ/ሮ ነጅሚያ ተናግረዋል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የኢኮቴ ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ፣ የመረጃ አያያዝን ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። የመረጃ ማደራጃ ሲስተም (ዳታቤዝ) ማልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ከበደ፣ የፕላት ፎርሞችን በራስ አቅም የማልማት ላይም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው የለማው ዳታቤዝ መረጃን ለማደራጀት የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል። የለሙትን ሲስተሞች በተገቢው መንገድ መጠቀም ይገባል ያሉት አቶ ደምስ፣ የውሸት ሪፖርትን በመቅረፍ ረገድ የሚኖራቸው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም አመላክተዋል። የመረጃ ማደራጃ ሲስተም (ዳታቤዝ) አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የክህሎት ስልጠና ከመዋቅር ለተውጣጡ ባለሙያዎች በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ነው።