
የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ባህል በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ እየተሰራ ነወ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለገበያ ማፈላለጊያ መንገድ አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ማስፋፋት የሚችል ሀገራዊ የምርምርና ኢኖቬሽን ወርክሾፕና የጉብኝት መርሃ ግብር አካሄደ። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሃብት ልማት ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉ/ቋ/ኮ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌኔጮ መንግስት የሀገራችንን ዜጎች ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን፣ የልማት እቅዶችን በማውጣትና እስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየሰራ መሆኑን አሰገንዝበዋል። ሀገራችን ትላልቅ ራዕዮችን ሰንቃ ህዝብን በማስተባበር የለውጥ ስራዎችን እየሰራች ነው ያሉት የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌኔጮ የምርምር ስራዎች ተመንዝረው የአብዛኛውን የአርሶ አደርና የከተማ ማህበረሰብ ህይወት እንዲቀየር በሁሉም ዘርፎች መፍትሔ የሚያመጡ ጥናትና ምርምሮች እየተሰሩ ነው ብለዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ በዓለም ላይ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ የህግ ማዕቀፍ፣መሰረተልማትና ምቹ ስነምህዳር የገነቡ ሀገራት በኢኮኖሚው ግንባር ቀደም መሆን አስችሏቸዋል ብለዋል። ነገን የተሻለ ለማድረግ በምርምና በኢኖቬሽን ላይ ከመስራት ውጪ አማራጭ የለንም ያሉት ሚኒስትሩ በተፈጥሮ ያሉንን ሀብቶች ለማሳደግና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ብሎም ለመጠቀም በቴክኖሎጂ ማገዝ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ በመተግበር ላይ ያሉ ሀገር አቀፍ የምርምር ስራዎች በማህበረሰቡ የኢኮኖሚ እድገትና በስራ እድል ፈጠራ ላይ የምንፈልገውን ውጤት በማምጣት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። የፕርግራሙ ተሳታፊዎች በገላን ከተማ ከምርምር ወደ ኢንዱስትሪ ያደገውን ባርግባ የወረቀት ማምረቻ የግል ድርጅት፣ በቢሾፍቱ የሚገኘውን ብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የስራ ውጤቶችና በተለያዩ ተቋማት የተሰሩ የምርምር ውጤቶች ላይ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ተዟዙረው ጎብኝተዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሃብት ልማት ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ከተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ የክልሎች የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፣ የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት፣ ከኢንዱስትሪና የምርምር ተቋማትና የዘርፉ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል።