Skip to main content
zena20

ክልሉን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ግብ ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ። (ወራቤ፣ ጥር 21/2017 ዓ/ም) ቢሮው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈጻጸም እና በቀጣይ ወራት ዕቅድ ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ መክፈቻ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደተናገሩት ቢሮው ክልሉን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የተጣለውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ ነው። ፈጠራና ዲጂታላይዜሽን ሁሉ-አቀፍና አካታች የፖሊሲ ዘርፎች ናቸው ያሉት አቶ ሰላሙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶአቸውን በአግባቡ መጠቀም ይገባልም ብለዋል። በኢኮኖሚው ረገድ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት እና በገበያ ትስስር እንዲሁም በማህበራዊውም የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በማረጋገጥ ለሀገር ብልጽግና ወሳኝ መሆናቸውን አቶ ሰላሙ ገልጸዋል። ለሀገር ደህንነትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ፈጠራና ዲጂታላይዜሽን ጉልህ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው አደጋና ቀውስን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ወሳኝ በመሆናቸው ዘርፉን ለማሳደግ ቢሮአቸው በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ለግማሽ ዓመቱ የተጣሉ ዋና ዋና ግቦች መሳካታቸውን አቶ ሰላሙ ጠቁመው የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ ይጠበቃልም ብለዋል። መድረኩ በአፈጻጸም የታዩ ጥንካሬዎችና ጉድለቶችን በመለየት ለቀጣይ ዕቅድ ግብዓት የሚገኝበትና መዋቅሮችም ልምድ የሚለዋወጡት መሆኑን ቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል። በመርሃ-ግብሩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን እያቀረቡ ሲሆን የቢሮው ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት ይደረግባታል ተብሎ ይጠበቃል።