Skip to main content
news2

ወራቤ፣ ጥር 17/2016 ስልጤ ዞን ኮሙኒኬሽን፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በድረ-ገጽ ልማትና አስተዳደር ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከክልል ከዞኑኖችና ልዩ ወረዳዎች የተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የሶፍትዌር ልማት ባለሙያዎች በወራቤ ከተማ አቶት ሆቴል መስጠት ጀምሯል፡፡

የስልጠና መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ባስተላለፉት መልዕክት ቴክኖሎጂን ማልማትና ጥቅል ተግባራት በዲጂታል ስርዓት እንዲመሩ ማድረግ በሀገር ደረጃ የታለመውን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ከግቡ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በመንግስት በኩል ለዜጎች የሚቀርቡ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ወጪና ጊዜን ቆጣቢ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል ስርዓቱ በሚገባ መስፋፋትና መታወቅ እንዳለበት ያነሱት አቶ ሰላሙ ይህን በማድረግ ሂደት የዘርፉ ባለሙያዎች ዘርፉን በሚገባ ተረድተው ሌሎችን በማሰልጠን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የዲጂታል ሲስተምና ሁሉን አቀፍ ቴክኖሎጂ በክልልና በሀገር ደረጃ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ እንዳይሆን ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የቢሮ ሀላፊው አስታውሰው ከዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች ጋር የሚተሳሰሩ ችግሮችን መፍታት ላይ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶን ጨምሮ የስልጤ ዞን ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊው አቶ ፈድሉ ጁሃርና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡

ስልጠናው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት በመጡ ከፍተኛ የሶፍትዌር ኤክስፐርቶች የሚሰጥ ሲሆን የስልጠናው መርሃ ግብርም ለሚቀጥሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡