Admin2
Tue, 11/03/2026 - 15:31
በዲጂታል ዘመን የሕዝብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍና የተቋማትን አሠራር ማዘመን እንደሚገባ ተገለፀ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ በዲጂታል ዘመን የሕዝብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍና የተቋማትን አሠራር ለማዘመን ያለመ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በሆሳዕና ከተማ መስጠት ጀምሯል።
ሥልጠናው በመንግሥት ሠራተኞች ዲሲፕሊን፣ የቅሬታ አቀራረብና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። ሥልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ፤ "ዓለም በሳይንስ፣ በኢኖቬሽንና በቴክኖሎጂ ፈጣን ለውጥ ውስጥ እያለፈ ነው" በማለት የአንድ ሀገርም ሆነ ክልል የልማት ደረጃና ተወዳዳሪነት በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በኢኖቬሽን አቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል። ኃላፊው አያይዘውም መድረኩ ከመደበኛ የሪፖርትና የውይይት መድረክነት ባሻገር የዘርፉን አቅምና ክፍተት የሚለይበት፣ የጋራ አቅጣጫ የሚቀየስበት፣ ተግባራዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበትና መልካም ተሞክሮዎች የሚለዋወጡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን እንደ አንድ መደበኛ የመንግሥት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የልማት ዘርፎችን አፈፃፀም የሚያፋጥን "የለውጥ ሞተር" አድርገን ማየት ይኖርብናል ያሉት አቶ ደምስ፤ የዘርፉ ሥራ በኮምፒውተር ጥገናና በኔትወርክ ዝርጋታ ብቻ ሳይገደብ የተቋማቱን አሠራር በማቀላጠፍ፣ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻልና የዜጎችን እርካታ በማረጋገጥ ላይ ማተኮር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሥልጠናው መድረክ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሀዲያ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ገነት ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችው ሆሳዕና ከተማ ውበቷና ድምቀቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል። አክለውም የሰላም አምሳደር የሆነችው ሆሳዕና ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ መዝናኛዎችና በቂ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያሏት በመሆኗ፣ እንግዶች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ከተማዋ በመምጣት እንዲጎበኙና እንዲዝናኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ የቢሮ ምክትል ኃላፊዎችን ጨምሮ የመሶብ አመራሮች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ኃላፊዎች፣ የሰው ሀብት ቡድን መሪዎች እና የሥነ ምግባር ፎካል ፖይንቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።