አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ የሥራ ርክክብ አደረጉ።
ወራቤ ፣መስከረም 26/2019 ፣ስልጤ ዞን ኮሙኒኬሽን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሆነው አዲስ የተሾሙት አቶ ደምስ ገብሬ ከቀድሞ የቢሮው ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ሰላሙ አማዶ ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል። እስካሁን በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችና በቀጣይ የለውጥ ዓመታት የሚተገበሩ የልማት ዕቅዶችን ለአዲሱ ኃላፊ የማስተዋወቅና የማስረከብ ሥራ ተከናወኗል።
በርክክቡ ወቅት የቀድሞው የቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰላሙ አማዶ ለአዲሱ ኃላፊ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚከናወኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ገለጻ አድርጓል። አቶ ሰላሙ አማዶ በቆይታቸው ከተቋሙ ማኔጅመንትና አጠቃላይ ሠራተኞች በመቀናጀት ያከናወኗቸውን የሥራ ስኬቶች የገለጹ ሲሆን አዲስ ለተሾሙት የቢሮው ኃላፊ መልካም የስራ ዘመንና የትጋት ጊዜ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የቢሮው ለአዲሱ ኃላፊ አቀባበል እና ለቀድሞው ኃላፊ ሽኝት ያደረገ ሲሆን የቢሮው ምክትል ኃላፊዎችና ማኔጅመንት አባላት በሰጡት አስተያየት የቀድሞ ኃላፊ ላበረከቱት አገልግሎትና ላከናወኑት የሥራ አፈጻጸም አድናቆታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ የሥራ ዘመን መልካም ስኬትን ተመኝተዋል።
አዲሱ የቢሮ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው፤ በሚኖራቸው ቆይታ ቢሮውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በሥራ ርክክቡ ወቅት የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች፣ የማኔጅመንት አባላትና እንዲሁም ጠቅላላ ሠራተኞች ተገኝተዋል።