በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የክረምት ስልጠና መስጠት ጀመረ። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለተከታታይ አንድ ወር የሚቆይ ሰፊ የክረምት ስልጠና መስጠት ጀምሯል። ስልጠናው በሳተላይት (Satellite Module Training); በሰው አልባ አውሮፕላን / ድሮን (UAV/Drone); በጂአይኤስ (GIS); በሮኬት ሳይንስ (Rocket Science); አስትሮኖሚ (Astronomy); በስፔስ እና ፕላኔተሪ ሳይንስ (Space and Planetary Science) ዘርፎች በሺዲዮ የተደገፈ እንደሆነ ተመላክቷል። ስልጠናው በክልሉ በሚገኙ 3 ዩኒቨርሲቲዎች (ወራቤ፣ ወልቂጤ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች) እንዲሁም በ10ሩም ዞንና ልዩ ወረዳ ማዕከላት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በስፋት እየተሰጠ ይገኛል። ከ2,500 በላይ ሰልጣኝ ተማሪዎች እና የፈጠራ ባለቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደገለፁት፣ ስልጠናው ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ የሚሰጥ ሲሆን ሰልጣኞች በቆይታቸው በስፔስ ሳይንስ፣ በጂኦ ስፓሻል እንዲሁም በኢኖቬሽን ዘርፍ ያላቸውን ንድፈ-ሀሳባዊ እውቀት ወደ ተግባራዊ የፈጠራ ክህሎት የሚያሳድጉበት በመሆኑ ክልላችንን የፈጠራ ማዕከል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።