Admin2
Sat, 08/01/2026 - 12:31
ከቴሌኮም ማስፋፊያ እስከ ሳይበር ደህንነት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ፤
በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ የሀገራትን ብልጽግና እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አቅም ዋነኛ መሣሪያ ሆኗል።
በአፍሪካ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በመገንዘብ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።
የቀደመውን "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ ስኬት ተከትሎ፣ ሀገራችን ወደ ቴክኖሎጂ እውቀት የተመራ ኢኮኖሚ የሚያሸጋግር እና በአፍሪካ የዲጂታል መሪ የሚያደርጋትን "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" መሪ ዕቅድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።
ይህ የዲጂታል አብዮት የዜጎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የአሠራር ግልጽነትን በመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን እና ብልሹ አሠራሮችን በመቀነስ በመንግሥትና በዜጎች መካከል ያለውን መተማመን ያጎለብታል።
በቴሌኮም ዘርፉ እየተካሄደ ያለው የ4G እና 5G ኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የቴሌኮም እና የባንኮች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እንዲሁም የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ)፣ የፓስፖርት እና የንግድ ፈቃድ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል መሸጋገራቸው ቢሮክራሲን በማስቀረት የፋይናንስ አካታችነትን እና የንግድ እንቅስቃሴን አቀላጥፈዋል።
በሌላ በኩል ዲጂታላይዜሽን የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሳይበር ምህዳርን ከጥቃት ለመከላከል እንደ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ በማገልገል ላይ ይገኛል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰራሮቻቸውን ወደ መረጃ መር እና ቴክኖሎጂ ታጋዥ መዋቅር በመቀየር ወንጀልን የመከላከል እና የድንበር ደህንነትን የማስጠበቅ አቅማቸውን አሳድገዋል።
አዲሱ የ2030 ስትራቴጂ በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትሕ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የቴክኖሎጂ ልዩነት የሚያጠብ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርግ ሀገራዊ የምስራች ነው።