Admin2
Fri, 07/31/2026 - 12:22
የማህበራዊ ክላስተር የብልፅግና ህብረት እና የቤተሰብ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በሆነ መልኩ ለማደራጀት እና ለማስተዳደር የሚያስችል ሲስተም ለማልማት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ተገለፀ።
"ዲጂታላይዜሽን ለዘመናዊ አደረጃጀት፤ ጠንካራ አባላት ለተሻለ የፓርቲ ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ የመረጃ አደረጃጀትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ለክላስተሩ የብልጽግና ቤተሰብ አመራሮች የተዘጋጀ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሂዷል።
የማህበራዊ ክላስተር የብልፅግና ህብረት እና የቤተሰብ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በሆነ መልኩ ለማደራጀት የሚያስችለው ሲስተም በክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ እንደሚለማ ተመላክቷል።
የስልጠና መድረኩን የመሩት የክልሉ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የወራቤ ክላስተር የብልፅግና ህብረት የአደረጃጀት ዘርፍ አመራር ወ/ሮ ነጅሚያ ራህመቶ እንዳሉት የፓርቲ አጠቃላይ መረጃዎችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለማደራጀት የሚለማው ሲስተም ጠቃሜተው ከፍተኛ ነው።
ሲስተሙ መረጃን በተገቢው ከማደራጀት አንፃር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን የሚቀርፍና በፍጥነትና ቀልጠፋ በሆነ አኳኃን መረጃን ዲጂታላይዝ አድርጎ በአግባቡ ለመሰነድ አጋዥ እንደሆነም ገልፀዋል።
"ከምርጫ መግስት ጠንካራ መንግስት" በሚል ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመላክተው ለዚህም ስኬታማነት በየዘርፉ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች የመረጠንን ህዝብ እርካታ በሚያሳድግ አኳኃን መሆን አለበት ብለዋል።
እንደ መንግስትና ፓርቲ ለዲጂታላይዜሽን የተሰጠውን ትኩረት ለማሳካት በየደረጃው የሚሰሩ ስራዎችን ዲጂታላይዝ እንዲሆኑ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የማህበራዊ ክላስተር የብልፅግና ህብረት እና የቤተሰብ መረጃዎችን በአጭር ሰዓት ወደሚለማው ሲስተም ለማስገባት በትኩረት መስራት እንደሚገባም ወ/ሮ ነጅሚያ አሳስበዋል።
የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው በቢሮው የሚለማው ሲስተም በማኑዋል ይደራጅ የነበረን የመረጃ አደረጃጀት ወደ ዲጂታል የሚቀይር ወቅቱን የዋጀ ስራ ነው ብለዋል።
ቢሮው ለበርካታ ተቋማት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሲስተሞችን እየለማ እንደሚገኝ ገልፀው ለማህበራዊ ክላስተር የብልፅግና ህብረት ቤተሰቦችን መረጃ በተደራጀ አግባብ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚለማው ሲስተም የዚያው አካል ነው እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሲስተሙ ሁሉንም መረጃዎችን በተሰናሰለ መልኩ የሚይዝ እና የህብረት ሰብሳቢው በሁሉም ቤተሰቦች እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን በቀላሉ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል እንደሆነም አቶ ሙህዲን ገልፀዋል።
አጠቃላይ ሲስተሙ የሚለማበትን ሂደት በተመለከተ እንዲሁም የቢሮውን የቤተሰብ ሲስተም ተሞክሮ የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ባለሙያ አቶ ሞላልኝ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
የስልጠና መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚለማው ሲስተም አስፈላጊነቱና ጠቃሜተው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በስልጠናው የወራቤ ብልፅግና ፓርቲ ህብረት የስምንቱም ቤተሰብ አመራሮች እና ሲስተሙን የሚየለሙ ቡድኖች ተሳትፈዋል።