Admin2
Thu, 07/30/2026 - 11:48
የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዋቅሮች የዲጅታል አሰራሮችና አዳዲስ ግኝቶች ዋነኛ ምንጭ መሆን እንዳለባቸው ተጠቆመ።
(ሆሳዕና፣ሀምሌ 23/2018)፣የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዋቅሮች የዲጅታል አሰራሮችና አዳዲስ ግኝቶች ዋነኛ ምንጭ መሆን አለባቸው ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የውይይት መደረክ ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ(ዶ/ር) በመስኩ ጠንካራ ተቋማት በመፍጠር በሁሉም ዘርፎች ዲጂታላይዜሽንን ለማስፋት ፈጠራን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል። ክልሉን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል። ዲጂታል ቴክኖሎጂ የአለም ሀገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ መሰረት በሆነበት በዚህ የውድድር ወቅት ዘርፉን ከሀገራዊ ኢኮኖሚ መጎልበት ጋር ማቆራኘት እንደሚገባም አስታውቀዋል ።
አሁን ላይ በቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ መግባቱ የግድ መሆኑን ያነሱት ልዩ አማካሪው በተለይ የዲጅታል ቴክኖሎጂን መላመድ፣ መፍጠን፣ በደንብ መረዳትና በአግባቡ መገዘብ ይሻል ብለዋል። በሀገራችን መሶብ፣ፋይዳና ዲጅታል ሲቪል ሰርቪስ ይህን የቴክኖሎጂ የግድነት በተለይም የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030ን የሚያሳዩ ኢንሼቲቮች መሆናቸውን አብራርተዋል ። የዲጅታል ስራ እድል ፈጠራ ጉዳይም ልዩ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ ዶ/ር ንጉሴ አስታውቀዋል።
የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ያለ ዲጂታላይዜሽን ከአለም ጋር አብሮ መራመድ ስለማይቻል ክህሎቱን ታጠቆ መወዳደር ወሳኝ ነው ብለዋል። እንደ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናዎችን ለስራ አጥነት መቅረፊያ መንገድ የማድረግ ጅምር እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ እንደሆነም አቶ ሰላሙ አስታውቀዋል ። በተለይም ሰልጣኖች ኦንላይን ስራዎች በንቃትና በብቃት ተሳትፈው የራሳቸውን የገቢ ምንጭና የኑሮ መሰረት እንዲመሰረቱ እያገዘ ነው።ይህም ብቻ ሳይሆን ብቃት ያላቸው ሰልጣኞች የውጭ ስልጠናና የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አስታውቀዋል።
መዋቅሩ የቴክኒካል ባለሙያዎች እጥረት፣ በተከታታይ ስልጠናዎች፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን ወደ ቢዝነስ መቀየር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ።
የክልሉን የሳይንስ፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ እምቅ አቅም አጉልቶ ማውጣት እንደሚገባም አቶ ሰላሙ ተናግረዋል። የዲጅታል አለሙን ግዙፍ የገንዘብ አቅም ወደ ሀገር ለመሳብ በሚያስችል መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል። የዲጅታል አሰራርን በማስፋፋት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የበኩላችንን እንወጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተነሳው ዜጎችን በዲጅታል እውቀትና ክህሎት የማብቃት፣ለዚህ አጋዥ የሆኑ ውጤታማ ስልጠናዎችን መስጠት ፣ከቴክኒክና ሙያ ኮሎጆች ጋር ቅንጅት መፍጠር ፣ለዲጅታላይዜሽን መጎልበት ቁልፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላትና ለወጣቶች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተነስቷል።
የዲጅታል ዘርፉ የምርጫ ሳይሆን የግድ በሆነበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ተቋማት ከዚህ ስርኣት ጋር ለመራመድ የሚያስችላቸውን እርምጃ መውሰድ እና ይህ ዘርፍ ሀብት እንዲፈጥር፣ የዜጎችና የሀገርን ኢኮኖሚ መቀየር እንዲችል ማድረግ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው በወቅቱ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ላይ በእቅድ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ጥሩ ውጤት ያመጡ መዋቅሮች የላፕ ቶፕ ኮምፒውተርና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም የዋንጫና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።