Admin2
Thu, 07/30/2026 - 11:45
የዲጅታል ቴክኖሎጂን የስራ እድል ፈጠራና ሁነኛ የኢኮኖሚ አማራጭ አድርጎ መጠቀም ይገባል- ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ።
(ሆሳዕና፣ ሀምሌ 23/2018)፣የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ባሳለፍነው በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የምክክር መድረክ በወራቤ እያካሄደ ነው።
የዲጅታል ቴክኖሎጂ ክህሎትና ፈጠራን በማጎልበት የስራ እድል ምንጭና ሁነኛ የኢኮኖሚ አማራጭ አድርጎ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናግረዋል ።
አቶ አንተነህ የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮን የምክክር መድረክ ሲከፍቱ እንዳሉት ዲጅታል ቴክኖሎጂ የወቅቱ ቁልፍ አቅምና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሆኖ ይገኛል።
ዘርፉ ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍቻ ሆኖ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።
በተለይም ከሙስና የጸዳ፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለህዝብ ለማቅረብ ሚናው አይተኬ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል ።
ዲጅታል ቴክኖሎጂ በአለም ዙሪያ የስራ አጥነት ችግርን በመቅረፍ ሰፊ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገራትንም ሆነ በባለጸጋዎች የኢኮኖሚ አቅም ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሆነ አብራርተዋል ።
ከዚህ መነሻ በዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅምን ማገልበት ምርጫ ሳይሆን አስገዳጅ ነው ብለዋል።
በክልሉ የዚህን ዘርፍ ፋይዳ ለማጎልበት በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል ። በተለይ ከዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ኢንሼቲቭ ጋር ተያይዞ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ግቦችን ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ አንተነህ አስታውቀዋል ።
ከዚህ አለም አቀፋዊ መነሻ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መወቅር የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅሞችን ማጎልበትና ማብቃት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ቡኩላቸው ዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ተግባራትን በማቀላጠፍ የተገልጋይ እርካታን በማሳደግ ላይ ይገኛል ።
ቢሮው በክልሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ላይ ከሌሎች መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት የድርሻውን ማበርከቱንም አስታውቀዋል ። እንደ ሴክተር የዜጎችን እንግልት በሚቀንሱና ቀልጣፋ የአሰራር ስርኣቶች እንዲዘረጉ በሚያግዙ የፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ሰላሙ በኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ በ2018 በጀት አመት ብቻ ከ235ሺ ሰዎች ስልጠናውን ለመከታተል ተመዝግበዋል ብለዋል። ከ185ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰልጣኞች ሰርተፍኬት እንደተሰጣቸው ሃላፊው አስታውቀዋል ።
ዘርፉ ለወጣቶች ጠቃሚ የስራ እድል እንዲፈጥርና የክልሉ ወጣቶች የዲጅታል ፈጠራ ክህሎት እንዲጎለብት በትኩረት መሰራቱንም አንስተዋል።
የስልጤ ዞን ምክትል ዋና አስተዳደሪ አቶ ሙበራ ከማል በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል ።