መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በመንግስታዊ ተቋማት ላይ ይስተዋል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግሮር በመቅረፍ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው አንዳንድ የሀላባ ቁሊቶ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
(ሆሳዕና፣ሐምሌ 22/2018)የክልሉ መንግስት አሰራርን በቴክኖሎጂ በማዘመን እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተገልጋዮች ጠይቀዋል አቶ አብዱል ከሪም ናስር የቁሊቶ ከተማ ነዋሪ ናቸው በከተማው በአጭር ጊዜ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ማዕከል ከዚህ ቀደም በመንግስታዊ ተቋማት ላይ ይስተዋል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግሮር በመቅረፍ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። ጉዳይን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነትን ከማስቀረት ባለፈ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን እንደሚያስችላቸውም ተገልጋቾ አብራርተዋል።
በከተማው ጉዳያቸውን እያስፈጸሙ ከነበሩ ተገልጋዮች መካከል አቶ ነስሩ መሐመድ እና ወ/ሮ መዲና ሙዴ ተጠቃሽ ናቸው ረጅም ርቀት ሳይጓዙ በአቅራቢያቸው በአንድ ጣራ ስር ሁሉንም አገልግሎቶች ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግስት አሰራርን በቴክኖሎጂ በማዘመን እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተገልጋዮች ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ በበርካታ መመዘኛዎች ሲታይ በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ የክላስተር ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማስገንባት ወደ ተግባር ስለመገባቱ ኃላፊው ጠቁመዋል። በክልሉ በ6 ማዕከላት ግንባታ በማጠናቀቅ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ያሉት አቶ ገብሬ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽነትን ለማስፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስራ የገባው የሆሳዕና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እስካሁን ከ33ሺ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንዳደረገም ኃላፊው ጠቅሰዋል። በክልሉ በወልቂጤ፣ በሆሳዕና፣ በሀላባ፣ በዱራሜ እና በሌሎችም ማዕከላት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘት ላይ ስለመሆኑም አቶ ገብሬ አስረድተዋል። በተለያዩ ከተሞች የተገነቡት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት አብይ አላማ የተገልጋዩን ማህበረሰብ እርካታ ማረጋገጥ ስለመሆኑም ኃላፊው ጠቁመዋል።
ለማዕከላቱ ስኬታማነት ክቡር ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)የቅርብ ድጋፍና ክትትል የነበረውን አበርክቶ አቶ ገብሬ በአብነት ጠቅሰዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ በሁሉም መስክ ለተጀመረው እድገት ስኬታማነት የጎላ ሚና አለው። የዜጎችን እንግልት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉልህ ሚና እንዳለውም አቶ ከበደ ጠቅሰዋል።
በክልሉ በ2019 በጀት አመት ዜጋ ተኮር አገልግሎቶችን ራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት ለመስራት መታቀዱን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የህብረተሰቡን ጊዜ፣ጉልበት እና ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ ለአዲስ የስራ ባህል መፈጠር ምክንያት ስለመሆኑም አቶ ከበደ ጠቁመዋል።