በክልሉ የህዝቡን ችግር ለመፍታት በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ :- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) (ሆሳዕና፣ ሰኔ 30/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በቡታጅራ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ስራ አስጀመሩ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በቡታጅራ ከተማ ተገንብተው ለምረቃ የበቁ ተቋማትን ስራ ባስጀመሩበት ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ በኋላ በክልሉ በዛሬው እለት ለ7ኛ ጊዜ ማስመረቅ ተችሏል ብለዋል። የክልሉ መንግስት ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማዘመን በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የህዝብን ችግር ለመፍታት እና ዘመኑን የዋጀ አመራር በመስጠት አዳዲስ ድሎችን እናስመዘግባለን ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለልማት ፕሮጀክቶች ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዘመናዊነት መገለጫ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
በከተማው ለምረቃ የበቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ላደረጉ አካላት በሙሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል። የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የኑሮ ውድነት ለማቃለል ከሰንበት እስከ ሰንበት የግብይት ማዕከል እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚያስችለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዞኑ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከሰንበት እስከ ሰንበት የግብይት ማዕከል ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በትብብር መገንባቱን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ የሚያቀላጥፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የበለጸገ ተቋም ስለመሆኑም ተናግረዋል። ህብረተሰቡ ባልተንዛዛ ቢሮክራሲ ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ የአገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል። ከዚህ ቀደም በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩ ተቋማትን ወደ ማዕከሉ በማስገባት በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መፍታት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
የተገልጋዩን ህብረተሰብ ጊዜ፣ጉልበት እና ገንዘብ ቆጣቢ ዲጂታል ማዕከል ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ስለመሆኑም አመላክተዋል። ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ እንደገለጹት የከተማዋን ህብረተሰብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መፍታት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመገንባት ለምረቃ ማብቃት ተችሏል ብለዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ዘመናዊ የግብይት ማዕከላት የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ የሚኖራቸው አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑም ከንቲባው ተናግረዋል። በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ብር ወጪ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶችን ለምረቃ ማብቃት መቻሉን ከንቲባው በአብነት ጠቅሰዋል። በ210 ሚሊየን ብር የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከል የከተማዋን ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ግልጽ ፣ ከአድሎ እና ጉቦ የጸዳ ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።