Skip to main content
zena109

ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ትብብር እና የላቀ ጥረት ይጠይቃል :- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) (ሆሳዕና፣ ሰኔ 19/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን የዱራሜ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ስራ ጀምሯል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ማዕከሉን መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ትብብር እና የላቀ ጥረት ይጠይቃል። ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና ለነበረው ለከምባታ ዞን ህዝብ እና አመራር ምስጋና አቅርበዋል።

በክልሉ በተለያዩ ከተሞች አምስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተመርቀው ስራ መጀመራቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የዱራሜ ከተማ ደግሞ 6ኛው ማዕከል መሆኑን ጠቅሰዋል። በዞኑ በሽንሽቾ እና በዶዮ ገና ከተሞችንም ማዕከላትን ለማስጀመር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዘመናዊነት መገለጫ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጊዜ ይቆጥባል፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ያስቀራል እንዲሁም አገልግሎትን የተቀላጠፈ ያደርጋል ብለዋል።

በክልሉ በተለያዩ ከተሞች የአውቶቢስ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም አመላክተዋል። የዱራሜ ከተማን ህዝብ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት 4 አመታት በቂ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፣ የመብራት የውሃ፣ የጤና ፣ የትምህርት፣ የመንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማሟላት ጠንክሮ መስራት ይገባል ብለዋል። መላው አመራሩ እና ህዝቡ ተቀናጅተው ከሰሩ ከ 8 እስከ 10 ቢሊየን ብር በሚደርስ ወጪ የከተማዋን ገጽታ መለወጥ ቀላል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።

ከደባል አጀንዳ በመውጣት ሙሉ ትኩረታችንን በልማት ስራ ላይ ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል። የከተማዋን የመብራት እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እውን ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። አካባቢው ለም እና ትርፍ አምራች መሆኑን ተከትሎ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ለማፋጠን የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ይገባል ብለዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ከእንግልት እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ነጻ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል። ከተሞችን ለኑሮ ለንግድ እና ኢንቬስትመንት ተመራጭ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል። በዞኑ ጸጋዎችን በመለየት መላውን የዞኑን ህዝብ በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ስለመቻሉም ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል። የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር እና ገበያውን ለማረጋጋት ከሰንበት እስከ ሰንበት የግብይት ማዕከላትን ስራ ማስጀመር መቻሉን በአብነት ጠቅሰዋል።

የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አክሊሉ አቡቶ እንደገለጹት የከተማዋን ህዝብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 247 ሚሊየን ብር በጀት በመመደብ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር ማድረግ መቻሉን ከንቲባው አስረድተዋል። በከተማዋ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አክሊሉ ጠቁመዋል።