Skip to main content
zena108

በህዝብ እርካታ ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ማጠናከር ይገባል :- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) (ሆሳዕና፣ ሰኔ 16/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)በሀላባ ቁሊቶ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ስራ አስጀምረዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት በህዝብ እርካታ ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግስታዊ አሰራርን ያዘምናል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። ተበታትነው ያሉ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መሰል የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የላቀ ጥረት ላደረጉ ለክልል፣ለዞን እና ለከተማ አስተዳደር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይ ለህብረተሰቡ ቤት ለቤት አገልግሎት መስጠት እንዲቻል የአውቶቢስ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው በዛሬው እለት ለምረቃ የበቃው ማዕከል የተንዛዛና የተበታተነ አገልግሎትን ማዘመን የሚያስችል ነው ብለዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመከባበር፣ የመተባበር፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል። ይህን ሀገር በቀል የትስስር ጥበብ ወደ ዘመናዊ የመንግስት መዋቅር አሰራር ውስጥ አጣምሮ በማስገባት የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥ የተቀላጠፈ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከድጂታል ሽግግር ባሻገር ለዘመናት በተንዛዛ የቢሮክራሲ ማነቆ ውስጥ የቆየውን አሰራር የሚያስቀር ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገመዳ መሀመድ እንደገለጹት የለውጡ መንግስት ለከተሞች እድገት በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል። ህብረተሰቡ ለረጅም ዓመታት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ጊዜውን፣ገንዘቡን እና ጉልበቱን ሲያባክን መቆየቱን ከንቲባው ጠቁመዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የህብረተሰቡን የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ ስለመሆኑም አቶ ገመዳ አብራርተዋል። ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ስር መስጠት የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል።