Skip to main content
zena108

በአጭር ጊዜ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገን በትብብር መስራት ብቻ ነው። ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር (ሆሳዕና፣ሰኔ 9/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ስራ አስጀምረዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )ማዕከሉን መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በአጭር ጊዜ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገን በትብብር መስራት ብቻ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ በተለያዩ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመመረቅ ስራ ማስጀመር መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። በቅርብ ቀን በሌሎች ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለምረቃ እንደሚበቁም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። በክልሉ የተያዘው በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ከ15 እስከ 17 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላትን ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል። የሚያስፈልገው መተባበር ብቻ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከደባል አጀንዳ በመውጣት ለጋራ እድገት መስራት ተገቢ ስለመሆኑም አሳስበዋል።

የሆሳዕና ከተማን ከሌሎች ትልልቅ ከተሞች ለማሰለፍ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ብቻ በቂ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣የንጹህ መጠጥ ውሃ፣የንግድ ማዕከላት፣ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን ለማሟላት 10 ቢሊየን ብር በመመደብ መስራት ከተቻለ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። የህዝብ ትብብር እና ድጋፍ ካለ አካባቢን መለወጥ እንደሚቻል የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢው ተወላጆች እና የንግዱ ማህበረሰብ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል። የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ እንዳሉት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማስፋፋት ረገድ የህዝቡ ድጋፍ የላቀ ነው ብለዋል። በዞኑ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

የሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ከማረጋገጥ ባለፈ ገቢን ያሳድጋል ብለዋል። ከሰንበት እስከ ሰንበት የግብይት ማዕከል የክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ኢኒሼቲቭ ነው ያሉት አቶ ማቲዎስ በዚህም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን አቅም ያገናዘበ ግብይት ይካሔድበታል ብለዋል። የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው በከተማው ተገንብተው ለምረቃ የበቁት ፕሮጀክቶች የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ነው። የሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ 220 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ የተደረገበት ስለመሆኑ የገለጹት ከንቲባው በዚህም የተገልጋዩን ህብረተሰብ ጊዜ፣ጉልበትና ገንዘብ ቆጣቢ ያደርገዋል። ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋል የመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሰራር በማስቀረት ረገድ የሚኖረው አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑም ከንቲባው አብራርተዋል።

በከተማው በዛሬው እለት ብቻ ከ335 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ የተደረገባቸው 8 የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አቶ ሳሙኤል አብራርተዋል።