Skip to main content
zena106

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ማዘመን ያስችላል :- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ሰኔ 8/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወልቂጤ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ስራ አስጀመሩ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )እንደገለጹት ልዩ ልዩ ተቋማትን ያካተተው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ያስችላል። በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ለምረቃ ይበቃሉ ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። በክልሉ 2018 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ከ15 እስከ 17 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

በወልቂጤ ከተማ በዛሬው እለት የተመረቀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ እንዲጀምር ድጋፍ ላደረጉ አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል። የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከወረቀት ንክኪ እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አሰራር መዘርጋት ያስችላል። የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ረገድ የሚኖራቸው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

ከተማዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጥ የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ተወዳዳሪነቷን ለማላቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ላጫ አብራርተዋል። የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ከተማዋ የአንድነት እና የታታሪ ህዝቦች መገኛ ነች ብለዋል። የንግድና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ማሳያ ከተማ ስለመሆኗም ከንቲባው አስረድተዋል። ከለውጡ መንግስት ወዲህ የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ነች ያሉት ከንቲባው በከተማዋ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ስኬታማ ያደርገዋል ብለዋል።