Skip to main content
Zena1111

የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በአዳዲስ
ሃሳቦቻቸውና በፈጠራ ስራዎቻቸው የበቁ ወጣቶችን መፍጠር ተገቢ ነው:-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ

(ሆሳዕና፣ሰኔ 5/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 3ኛው ዙር የሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድርና ዓውደ-ርዕይ በቡታጅራ ከተማ ተመርቆ ለዕይታ ክፍት ሆነ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በአዳዲስ ሃሳቦቻቸውና በፈጠራ ስራዎቻቸው የበቁ ወጣቶችን መፍጠር ተገቢ ነው ብለዋል።

የሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድርና ዓውደ-ርዕይ ከክልሉ የተውጣጡ ከ146 በላይ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች በስምንት ዋና ዋና የውድድር ምድቦች ቀርበዋል ብለዋል።

በ2018 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገራዊ የፈጠራ ውድድር ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 2ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።

ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበው ውጤት ለ3ኛው ዙር ውድድር ትልቅ መነቃቃትንና ብርታትን መፍጠሩን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የተሻለ ተወዳዳሪ ሆነን እንድንገኝ ከፍተኛ ሀላፊነት ሰጥቶናል ብለዋል።

ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ዓለማችንን የቀየሩት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተወለዱት በቤተ-ሙከራዎች ብቻ አልነበረም ያሉት አቶ አንተነህ የችግርን ቀንበር ለመስበር ሌሊትና ቀን በጨለማ ክፍላቸው ውስጥ ተቀምጠው ባሰቡ አካላት አእምሮ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እምቅና ብሩህ አዕምሮ ያላቸው በርካታ ወጣቶችና ህዝብ ባለቤት ነው ያሉት ኃላፊው ይህን እምቅ የሰው ኃይል አቅም በመጠቀም፤ የወጣቶቻችንን ያልተገደበ ምናብ እና የእጆቻቸውን ጥበብ ወደ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለመቀየር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ካለፉት ዓመታት እጅግ የላቁ፣ ይበልጥ ማህበረሰባዊ ችግሮችን በቀጥታ የሚፈቱ፣ ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ተሻግረው የህዝቡን የዕለት ተዕለት ህይወት ማሻሻል የሚችሉ ስራዎች መቅረባቸውን በተግባር የምናይበት ነው ብለዋል፡፡

የፈጠራ ሥራዎችን ከዕውቀት ማፍለቅ ጀምሮ እስከ ሥራ ዕድል ፈጠራና ወደ ገበያ ማውጣት ያለውን ሰንሰለት ሙሉ የሚያደርግ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ኃላፊው በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የፈጠራ ስራው የክልሉን ግብርና፣ አይሲቲ፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ጤና እና ትምህርት ዘርፍ ሊያዘምን የሚችል ትልቅ አቅም አለው ብለዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን እንዳሉት ሀገራት በኢኮኖሚ፣በቴክኖሎጂ እና በወታደራዊ አቅም ይወዳደራሉ ብለዋል።

የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ኢኖቬተርስ ማበረታታት፣መሸለም እና ማትጋት ለዘርፉ እድገት የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

በኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር )በበኩላቸው ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ በእውቀት፣በኢኖቬሽን በቴክኖሎጂ እና ከስራ ፈጠራ ጋር በማጣመር መስራት ተገቢ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የላቀ ሚና እንዳላቸውም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት በዘርፉ በተደረገ ጥረት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል፣ተወዳዳሪነት እንዲያድግ ማገዝ፣ማህበራዊ ተግዳሮት መፍታት፣ከድህነት መውጫ መሳሪያ በመሆን እንደሚያገለግል ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንደገለጹት
ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሀድ ችግር መፍታት ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች የፈጠራ ስራዎችን ማሳያ ብቻ ሳይሆኑ የሀገራችንን ኢንዱስትሪ እና የዲጂታል ስርዓት መጻኢ እድል ለሚቀረጽበት መንገድ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

መርሐ ግብሩን የትምህርት ቢሮ፣ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ በጋራና በከፍተኛ ቅንጅት ያዘጋጁት ስለመሆኑም ተመላክቷል