Skip to main content
Zena

‎ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በሳይንስ፣በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው :-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ 

‎(ሆሳዕና፣ሰኔ 4/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ውድድር አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ከሰኔ 5 እስከ 6 /2018 በቡታጅራ ከተማ ይካሔዳል። 

‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ለመገናኛ ብዙሀን በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በሳይንስ፣በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

‎ሳይንስ፣ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ለአንድ ሀገር ብልጽግና መረጋገጥ ወሳኝ ናቸው ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። 

‎ክልሉን የሳይንስ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ በሚል መሪ ቃል ለሁለት ተከታታይ አመታት የፈጠራ ስራ ውድድር አውደ ርዕይ መካሔዱን አስታውቀዋል። 

‎በክልሉ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ውድድር አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ከሰኔ 5 እስከ 6 /2018 በቡታጅራ ከተማ እንደሚካሔድ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። 

‎በክልሉ በማኑፋክቸሪንግ፣በግብርና፣በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በሌሎችም የልማት ዘርፎች የሚያጋጥሙ መዋቅራዊ ችግሮችን በሀገር በቀል እውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም አቶ አንተነህ በአብነት ጠቅሰዋል። 

‎ይህን አላማ ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ተማሪዎችን፣መምህራንን እንዲሁም ወጣቶችን ለማበረታታት 3ኛ ዙር ክልላዊ የሳይንስና ፈጠራ ውድድር እና አውደ ርዕይ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። 

‎ካለፉት ሁለት ዓመታት አንጻር ሲታይ የዘንድሮው  የሳይንስ የፈጠራ ውድድር እና አውደ ርዕይ ልዩ ገጽታ እንዳለውም አመላክተዋል። 

‎በመርሐ ግብሩ ሰፊ የምርምር ስራዎች ስብጥር እንደሚታይበት የገለጹት ኃላፊው 146 የፈጠራ ስራዎች እና ቴክኖሎጂዎች ለውድድር እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል። 

‎በመርሐ ግብሩ 8 የተለዩ የውድድር ዘርፎች የሚኖሩ ሲሆኑ ከ7ኛ እስከ 8 ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች፣ከ9ኛ እስከ 10ኛ፣ከ11ኛ እስከ 12 ኛ ክፍል ተማሪዎች፣የመካከለኛ ደረጃ የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል መምህራን፣ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን፣ኢንተር ፕራይዞች፣በግል የፈጠራ ውድድር እንዲሁም የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የፈጠራ ስራዎቻቸውን አቅርበው የሚወዳደሩበት ምድብ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል። 

‎ዘንድሮ ለውድድሩ የተለየ ትኩረት  በመስጠት እና ፍትሀዊ እና ሚስጥራዊ  እንዲሆን  ጥረት መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው ለዚህም የዋቸሞ፣የወልቂጤ እና የወራቤ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሁም የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መምህራን በዳኝነት እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል። 

‎ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች ልዩ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ያሉት አቶ አንተነህ በዚህ አውደ ርዕይ እና የፈጠራ ስራዎች ውድድር ላይ የቀረቡ ስራዎች ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ይሰራል ብለዋል። 

‎የተሻለ የፈጠራ ስራዎችን ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች ችግር ፈቺ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ምርት መግባት እንዲችሉ የገበያ ትስስር ይፈጠራል ያሉት ኃላፊው በፈጠራ ስራቸው የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ማግኘት እንዲችሉ ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አንተነህ አስታውቀዋል። 

‎የክልሉ ህዝብ፣ባለሀብቶች፣ተመራማሪዎች፣ወጣቶች የሚዲያ አካላት የክልሉን የፈጠራ አቅም እንዲመለከቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል