በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ስራ ለሚጀምረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዘርፉ የተመደቡ ባለሙያዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም ጋር የልምድ ልውውጥ አደረጉ ።
በልምድ ልውውጡም በተቋሙ ስለ ምሰጡ አገልግሎቶች ገለፃ የሰጡት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ ሲሆኑ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የግለሰቦችን የመረጃ ነፃነት በመጠበቅ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል ። ለተጠቃሚዎችና ለአገልግሎት ሰጪዎች ለስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመሶብ የመጀመሪያ ተግባር መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ለዚህም በትብብርና በቅንጅት መሰራት እንደሚገባም ለባለሙያዎቹ ገልጸዋል ።
ማዕከሉ በውስጡ ዘመናዊ የሆኑ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎችን ያሟላ አገልግሎት መስጫና የቅሬታ ማቅረቢያ ቴክኖሎጂዎች ያሉበት፣አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን ታሳቢ ያደረገ የእናቶችና ህፃናት ማረፊያን ጨምሮ ሁሉ አቀፉ አገልግሎት በውስጡ ስላለ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላልም ብለዋል ። የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አጀቡሽ ዋካልቶ በበኩላቸው ባለሙያዎች በስልጠናና በምልከታ ያገኙት ዕውቀትና ክሂሎት ወደ ተግባራዊ በመቀየር በከተማው በቅርቡ በሚጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህዝባቸውን በቅንነት፣በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገል እንደሚገባ ገልጸዋል ።
ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባ በተለያዩ ቦታዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ስለሚሰጥ የህዝቡን ጊዜ፣ጉልበትና የገንዘብ ወጪን ጭምር በመቀነስ ፈጣን አገልግሎት ለማስጣት ሲለሚያስችል በተገልጋዮች ዘንድ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ እንደሚፈጥርም አክለዋል። በመጨረሻም አስተያየት የሰጡት የዘርፉ ባለሙያዎች በማዕከሉ በተከለከሉና በሚፈቀዱ ተግባራት ላይ በማተኮር የተጣለባቸውን የህዝብና የመንግስትን አደራ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።