Skip to main content
zena95

ጤና ተቋማት የሚጠቀሙትን የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ብቃትና ደህንነት በየግዜው በማስፈተሽና ህግና አሰራር ተከትለው በመስራት የማህበረሰቡን ጤና ደህንነት መጠበቅ እንዳለባቸው ተገለጸ። መጋቢት 4/2018 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤናና ጤናነክ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በጤና ተቋማት የጨረራ አመንጪ የሆኑ የህክምና መሳሪያዎች ላይ ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን የቁጥጥር ስራዉ ግኝቶች በጋራ ተገምግሟል። በዚህ ግምገማ ወቅት የቁጥጥሩ ዋና አላማ ጨረራ አመንጪ የሆኑ የህክምና መሳሪያዎች የሚያመነጩት ጨረራ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እየተጠቀሙ መሆኑን እና መሳሪያውን የሚጠቀሙ ቴክኒካል ባለሙያዎች እና ታካሚዉ ላልተፈለገ ጨረር በማይጋለጥበት የአሰራር ስርዓት እየተጠቀሙ መሆኑን ቁጥጥር ማድረግ እንደነበረም ተመላክቷል።

የቁጥጥር ስራዉ በክልሉ ዉስጥ በሚገኙ 14 የግል ክሊኒኮችና የመንግስት ሆስፒታሎች ላይ የተሰራ ሲሆን በቁጥጥሩ ወቅት ትኩረት ተሰጥቶ ለማየት የተሞከረው በተቋማት ዉስጥ የሚገኘዉን የጨረራ አመንጪ መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ሁኔታ፣ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዉ ፈቃድና እድሳት ሁኔታ፣ የመሳሪያዉ አገልገሎት ምርመራ (Performance evaluation) ሁኔታ፣ የቴክኒክ ባለሙያ የጨረራ ተጋለጭነት መጠን ልኬት፣ አፈትላኪ ጨረር ስለመኖሩ እና ሌሎች አላስፈላጊ የጨረራ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ የአሰራር ሂደት ስለ መዘርጋቱ ፣የጨረራ መከላከያ ቁሳቁስ ስለመኖሩና የአጠቃቀም ስርዓቱ ምን እንደሚመስል እና ቀድሞ በተሰሩ የቁጥጥር ግኝት ግብረ መልስ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ምን እንደሚመስሉ በቁጥጥሩ የታዩ ጉዳዮች መሆናቸው በሪፓርቱ ተመላክቷል።

በቅንጅት በተሰራው ቁጥጥር ወቅት መሰረታዊ ጉድለት በነበረባቸው ሁለት ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ(ማሸግ) የተወሰደ ሲሆን 7 የሚጠጉ ተቋማት ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል እንዲሁም ከዚህ ግምገማ በኋላ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው ተቋማት እንደሚኖሩም በግምገማው ወቅት ተገልጿል። የታዩት ጤና ተቋማት ያሉባቸዉን ክፈተቶች በተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ማሻሻል እንዲችሉ የተጠናከረ ክትትል እንደሚያስፈልግ የባለስልጣኑ ዋና ዳይረክተር አቶ ፋሲካ አለሙ የገለጹ ሲሆን የተሰጣቸውን ግብረመልስ በተገቢው በማያስተካክሉ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል። አቶ ፋሲካ አለሙ አክለውም የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር በቅንጅት ለሚሰራቸዉ ስራዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም በተለያየዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን ባቴኖ እንዳመለከቱት የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ያሉባቸዉ ጤና ተቋማት ተገቢዉን የአገልግሎት ምርመራ በማድረግ በየጊዜዉ ፈቃድ ማሳደስ እና የባለሙያዉን እና ተካሚዉን የተጋላጭነት መጠን በሚቀንስ መልኩ መስራት እንዳለባቸዉ አመላክተዋል።

በሂደቱ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮዉ እገዛ እንደሚያደርግም የገለጹ ሲሆን መሰረታዊ ችግር ባለባቸው ተቋማት ላይ ቀጣይነት ያለው ቁጥጥር እንደሚደረግና በቅንጅት ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የጤናና ጤናነክ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ባለሙያዎችም ተገኝተዋል።