Skip to main content
zena94

ክልላዊ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ጭምጭምታ መሰብሰቢያ በይነ መረብ ተዘጋጀ፤ መጋቢት 4/2018ዓ.ም ‎ ‎ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያስለማው የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ጭምጭምታ መሰብሰቢያ በይነ መረብ ርክክብ ተካሄደ። ‎ ‎ክልላዊ የጤና በይነ መረብ ርክክብ ያካሄዱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እና የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ናቸው። ‎ ‎በርክክብ ፕሮግራሙ የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ በየጊዜው የሚነሱ ወረርሽኞችን በብቃት የመከላከል አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። ‎ ‎

በዘርፉ ትልቅ መሻሻሎች መምጣታቸውንም ጠቅሰው፣ለአብነትም በቅርብ ዓመታት ማልበርግ፣ኮሌራ፣ወባና የመሳሰሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የተደረጉ ርብርቦች ውጤታማ እንደነበሩም አመላክተዋል። ‎ ‎ሆኖም በስራዎቹ ላይ ወቅታዊ የወረርሽኝ መረጃ ቀድሞ የማግኘት ችግሮች እንዳሉም አመላክተዋል ፣እነዚህን ችግሮች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። ‎ ‎ይህንን ችግር ለመፍታትም ዛሬ ርክክብ የተደረገው በይነ መረብ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም የገለጹት አቶ ማሙሽ፣ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ቀድሞ የወረርሽኝ መረጃ በማሰባሰብ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የላቀ እገዛ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።

‎ ‎በይነ መረቡ የክልሉን ወረርሽኝ የመመከት አቅም የሚያሳድግ፣የመረጃ መዘግየትን የሚያስቀር፣ ‎ለህብረተሰቡ በቀላሉ ተደራሽ የሚሆን፣በክልሉ ሁሉም መዋቅሮችና ከሌሎች አካባቢዎች ጭምር የሚከሰቱ የወረርሽኝ ስጋቶችን ቀድሞ በመገንዘብ የህብረተሰብ ጉዳትን በከፍተኛ ደረጃ መቀንስ ያስችላል ብለዋል አቶ ማሙሽ። ‎ ‎የለማው ቴክኖሎጂ የሪፖርት መዘግየትን የሚያስቀር፣ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል ፣በእያንዳንዱ ቀበሌና ጎጥ ያለውን አጠቃላይ የወረርሽኝ መረጃ በፍጥነት የሚገልጽ፣ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ የሚያስችል እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። ‎ ‎

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የመረጃ ዘላቂነትን በቀጣይ የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ገልጸዋል። ‎ ‎የለማው በይነ መረብ በክልሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲጠናከሩ የሚያደርግ፣ጊዜና ወጭን የሚቀንስ፣ ‎የመረጃ ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እንዳለውም ቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል። ‎ ‎ቴክኖሎጂው ህብረተሰቡን ከወረርሽኝ እንዲጠበቅ ትምህርት መስጠት የሚያስችልና ጤናውን በመጠበቅ በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን እንዲችል ጥሩ አማራጭ ስለመሆኑም አቶ ሰላሙ ገለጻ አድርገዋል። ‎ ‎በይነ መረቡ የለማው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በመተባበር ነው።