Skip to main content
zena92

በኢትዮጵያ የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግ እና ወጣቶችን ለወደፊቱ የስራ ገበያ ለማዘጋጀት ታስቦ የተጀመረው የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ለሰዎች ዘመኑን የዋጀ እውቀትን እያለበሳቸው ነው፡፡

በዲጂታል ምህዳሩ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያደርገው ይህ የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም የታጠቁት እውቀት ለአዳዲስ ዕድሎች በር ከፋችም ሆኖላቸዋል። 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን በኮዲንግና በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሰለጥኑ በሚያደርገዉ ኢኒሸቲቭ የእድሉ ተጠቃሚ የሆነችው ተማሪ ኢክረም ከድር አንዷ ናት፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ኢክረም ከድር መንግስት እድሉን ሲያመቻች ለመጠቀም ወደኋላ አላለችም፡፡ ከትምህርቷ ጎን ለጎን የኢትዮ ኮደር ስልጠናን ተከታትላለች፡፡ ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመራመድ ፕሮግራሙ አጋዥ ነው የምትለው ተማሪ ኢክረም አሁን ላይ ለትምህርቷ፤ ወደፊትም ለመሆን ለምትፈልገው መሻቷ መሠረት ጥሎልኛል ብላለች፡፡

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ያሉ የመንግስት ሰራተኞችም በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ ለምናከናውነው ተግባር ትልቅ እገዛ አድርጎልናል ብለዋል፡፡ ከወረቀት አሰራር እየተላቀቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን መውሰድ ብዙ እንደሚያተርፍም ይናገራሉ፡፡ የ5 ሚሊየን ኮደርስ ፕሮግራም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ወጣቶች ፣ የመንግስት ሰራተኞችና በሌሎች የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች እንደተመዘገቡ የሚያነሱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ከ157 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ ተቋማት አገልግሎታቸውን ዘመናዊ ፣ የተቀላጠፈ እና የተደራጀ ለማድረግ እያስቻላቸው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰላሙ በርቀት የስራ እድል ፈጠራ ረገድም ጅምር ጠቀሜታ ማሳየቱን ጠቅሷል፡፡ ወጣቶች ወሳኝ የሆነውን የዲጂታል ክህሎት ሊቀስሙ ይገባል የሚሉት ሃላፊዉ አቶ ሰላሙ አማዶ ለተያዘው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላቅ ያለ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ እየታየ ያለው ተጨባጭ አካሄድ ለዚህ ማሳያ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡ የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም በኢፌዲሪ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ትብብር እየተተገበረ ያለ ሲሆን አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በኮዲንግና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማሰልጠን ላይ ያተኮረ ነው፡፡