Skip to main content
zena91

በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ ለሚተገበሩ ስራዎች ውጤታማነት የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው: ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ። በክልሉ የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ ለሚተገበሩ ስራዎች ውጤታማነት የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭ የሌለው ዘርፍ ነው ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል። የሀገር፣ የተቋም ብሎም የግለሰብ ተወዳዳሪነት የተመሰረተው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለተግባራዊነቱ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁነት ይጠይቃል ብለዋል።

በክልሉ የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ውጤታማ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ አንተነህ በዘርፉ ስልጠና የሚወስዱ ዜጎችን ቁጥር ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራት ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል። በየደረጃው ያለው አመራር በላቀ ቁርጠኝነት በመስራቱ ለኢኒሼቲቩ አፈጻጸም ውጤታማነት በምክንያትነት ተጠቃሽ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በአብነት ጠቅሰዋል። በክልሉ የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እስከ መጋቢት 30/2018 ድረስ የአመቱን እቅድ ለማሳካት መስራት ተገቢ መሆኑን ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ያመላከቱት።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ በተለይ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል። በክልሉ የመማር ማስተማር ስራው የዲጂታል ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉም አብራርተዋል። ለዘርፉ ስኬታማነት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ማሟላት አብይ ጉዳይ መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል። በዲጂታል ቴክኖሎጂ የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትምህርት ተቋማት ላይ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በኦንላይን ለማስፈተን የያዘውን አቋም በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል። የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ ያለውን ጠቀሜታ አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሀን ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አቶ አንተነህ አብራርተዋል። በመድረኩ የየም ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ቸርነት ሰውነት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በውጭ ሀገር ካምፓኒዎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስመልክቶ ልምዳቸውን አካፍለዋል።