በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከ157ሺ በላይ ዜጎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘታቸው ተመላከተ። በክልሉ የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደገለጹት በ5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከ157ሺ በላይ ዜጎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አግኝተዋል። አለም በፍጥነት ወደ ዲጂታል ዘመን እየተሸጋገረ ነው ያሉት ዓላፊው ይህን ተከትሎ የሀገራት ኃይል በቴክኖሎጂና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል። ዜጎቻቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያስታጠቁ ሀገራት ውጤታማ ስለመሆናቸውም ኃላፊው አስረድተዋል። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የተጀመረው የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች የዲጂታል ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አቶ ሰላሙ አብራርተዋል። በክልሉ ከ200ሺ በላይ ወጣቶች እና የመንግስት ስራተኞች ተመዝግበዋል ያሉት ኃላፊው ከነዚህ ውስጥ ከ157ሺ በላይ ዜጎች የብቃት ማረጋገጫ አግኝተዋል። በስልጠናው የብቃት ማረጋገጫ ከማግኘት ባለፈ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ስራ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን እየቻሉ ነው ሲሉም በአብነት ጠቅሰዋል። ቨመድረኩ ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና በአፈጻጸም ረገድ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አስረድተዋል። በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ ከክልል፣ከዞኖች እና ከልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።