Skip to main content
newa15

ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመን የተሻለ አገልግሎት መስጠትና ብልሹ አሠራርን በመከላከል የመንግስትን ሀብት ለመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ። ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመን የተሻለ አገልግሎት መስጠትና ብልሹ አሠራርን በመከላከል የመንግስትን ሀብት ለመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ። ኮሚሽኑ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በሆሳዕና ከተማ ተፈራርመዋል ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ በስምምነቱ ወቅት እንደገለፁት የተቋማትን ተልዕኮ በቴክኖሎጂ በመደገፍና አሰራርን በማዘመን በግልፀኝነት ተጠቃሚውን ሕብረተሰብ ማገልገል ይገባል ብለዋል። የስነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት ለማሳወቅ ለማስመዝገብና ሙስናና ብልሹ አሰራርን በዲጂታል ለመከታተልና ለመከላከል የሚያስችል ድረገጽ በማልማት ዜጎች ባሉበት ሆነው ጥቆማ እንዲሰጡ፣ ሀብታቸውን እንዲያሳውቁና እንዲያስመዘግቡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል። ተቋሙን በቴክኖሎጂ መደገፍ ከዚህ በፊት የነበረውን አሰራር በማዘመን የተሻለ አሠራር በመዘርጋትና ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነር ማሞ፥ ሁሉም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በእጁ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። ኢትዮጵያን በ2030 ዲጂታላይዝ ለማድረግና ዓለም በቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ለማድረስ መንግስት ሰፊ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ናቸው ። ተቋማት ከተለመደው አሠራር ወጥተው ዲጂታላይዝ ሆነው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ፥ ቴክኖሎጂው ጊዜ ጉልበትና ወጪ ከመቀነስ ባለፈ የሥራ ጫናን ቀላል ያደርጋል ብለዋል። ሶፍትዌር በማበልጸግና ድረገጽ በማልማት ተቋማት ከወረቀት ነጻ የሆነ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሰላሙ ተቋማት ቴክኖሎጂውን በአግባቡ በመጠቀም መረጃን ዘላቂና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ። በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የስነምግባር ት/ት ስርጭት አውታሮች ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር ኑሪ ከድር፥ የሀገራችን የፀረሙስና ትግልና ሀብት የማስመዝገብ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ስምምነቱ የተሸለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በኩል በድረገጹ ዙሪያ ማብራርያ የተሰጠ ሲሆን ከሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ተሰጥቶ የክልሉ ስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ እና የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ከአቶ ሰላሙ አማዶ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የውል ሰነድ ተፈራርመዋል።