Skip to main content
zena83

የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ብቁ እና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ስርአት እንዲገነባ ልዩ ሚና እንዳለው ተገለጸ። የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎች በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን በማገዝ የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ብቁ እና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ስርአት እንዲገነባ ልዩ ሚና እንዳላቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሄዷል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንሰና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠላሙ አማዶ፥ የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎች በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን በማገዝ የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ብቁ እና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ስርአት እንዲገነባ ልዩ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ክልሉን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፥ ያሉ ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ 22 ድረ-ገጾችን (ዌብሳይቶችን)እውን ማድረግ እንደተቻለም ተናግረዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነውን የ5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን በሚመለከት በግማሽ አመቱ 94ሺህ 448 ወጣቶችን እና የመንግስት ሠራተኞች በማስመስገብ ፕሮግራሙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉም 189 ሺህ 738 ወጣቶችን እና የመንግስት ሠራተኞች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም ውስጥ ከ 147 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀው የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን አክለውዋል።

በ2025 ስትራቴጂ የተገኙ መሠረቶችን ማስፋፋት ላይ ልዩ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፥ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የመረጃ ሉአላዊነት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ገዢ ሳትሆን ቴክኖሎጂ አምራች እንድትሆን የሚያስችል ዓላማ ሰንቆ የተቀረጸ መሆኑን ገልጸዋል። ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችል በክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተጀመረ እንደሆነ በማንሳት በቀጣይም በ17 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ሠላሙ አስረድተዋል።

አቶ ኑርልኝ ኮኩ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የክልሎች እና የካውንስሎች ጉዳይ ሀላፊ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ሴክተሮችን ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል። የሳይንስ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ጉዳይ ዲጂታል ስታርት አፕ በአንድ ተቋም ብቻ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም ያሉት ሀላፊው፥ ዘርፉ ተሻጋሪ (ተቋም ተሻጋሪ) መሆኑን በመግለጽ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች እና ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በመሆን መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሙህዲን ሁሴን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ እና የሳይንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስርጸት ዘርፍ ሀላፊ፥ ባለፉት 6 ወራት ለዲጅታል 2030 መሠረት የሚጥሉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ሲስተሞችን በማልማት፣ ድረ-ገጾችን በማበልጸግ እና በመንግስት ተቋማት ላይ በመተግበር የሚሠጡ አገልግሎቶችን ዲጂታል ለማድረግ መሠረት እየተጣለ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም "ክልሉን የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ማዕከል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ የቴክኖሎጂ ዲጂታል ሊትረሲ ስልጠና፣ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መስጠት እና የፈጠራ ስራ ባለቤቶችን ለማበረታታት እየተሠራ ነው ብለዋል። አክለውም በ6 ወር አፈጻጸምም እሄንኑ በማጠናከር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በመጨረሻም ከሁሉም የክልሉ መዋቅሮች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ጥያቄ እና አስታየቶች ተነስተው ውይይት በማድረግ በ 2018 በግማሽ በጀት አመት የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም የ2025 ስትራቴጂ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት ለዲጂታል 2030 አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል።