ተረጋገጡና ተዓማኒነት ያላቸው ክልላዊ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል የመረጃ ቋት ይፋ ተደረገ።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላን ልማት ቢሮ ከክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመሆን የለማ የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ ዌብ-ሳይት ርክብክብ ተደርጓል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በሰጡት ሀሳብ በክልሉ መንግስት የፀደቁና የተረጋገጡ ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎችን ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሰርቨር ከዌብ-ሳይት ጋር ማገናኘት ተችሏል። የለማው ዌብ-ሳይት ግለሰቦችም ሆነ ደርጅቶች ተዓማኒነት ያለው ክልላዊ መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት መሆኑን አንስተዋል። የክልሉን አጠቃላይ መረጃ ማደራጀትና መተንተን የቢሮው ዋነኛ ተግባር መሆኑን ኃላፊው አንስተው ይፋ የተደረገው ዌብ-ሳይት የመረጃ አያያዝን ለማዘመን አጋዥ ነው ብለዋል። በክልሉ ያለውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማዘመን በዘላቂነት የተደራጁ መረጃዎችን ለማግኘት የመረጃ ቋቱ አጋዥ መሆኑን አቶ ዳንኤል ጠቅሰዋል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በዚህ ወቅት ዲጅታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው ሶፍት ዌሮችን በማልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ቀዳሚው ተግባር ነው ብለዋል። የለማው ዌብ-ሳይት የወረቀት አሰራርን በማስቀረት የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በማዘመን በቀላሉ መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል። በዌብ-ሳይቱ በክልሉ ያለውን አጠቃላይ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ኃላፊው አንስተው የሁሉም ተቋማት ዕቅድ ፣ አፈፃፀምና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለመረዳት ያግዛል ነው ያሉት።