በቴክኖሎጂ የታገዘና በዲጂታል ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ብዝሃ ኢኮኖሚ የመገንባት ተልዕኮን ለማሳካት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ድርሻ ጉልህ ነው- የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ (ሆሳዕና፣ ጥር 18/2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የክልሉ ተቋማት የበጀት አመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አራተኛ ቀን ቀጥሏል። ቋሚ ኮሚቴው በዛሬው እለት የክልሉን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የ2018 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል። የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ለቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አቅርበው፣ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች የቢሮው የስራ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራ በግምገማ መድረኩ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና በዲጂታል ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ብዝሃ ኢኮኖሚ የመገንባት ተልዕኮን ለማሳካት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ድርሻ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል። ቢሮው በክልሉ የዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግር መሠረትን እየጣለ መሆኑን መገምገም ተችሏል ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ከወረቀት ነፃ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። የዲጂታል እውቀት ጥራትና ተደራሽነት፣ የተቋም ግምባታ፣ የፈጠራ ባለቤቶችን በእኩል መደገፍ እና ክልላዊ ኢንኩቤሽን ማዕከል ግንባታ ላይ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም አቶ ግዛቸው አመላክተዋል። የክልሉ ሳይስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ፣ የፈጠራ ስራዎችና ሀሳቦች ወደ ኢኮኖሚው ገብተው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኙ ለማድረግ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል። ዲጂታላይዜሽንን የሚያግዙ ስራዎችን ለመፈፀም በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተው፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።