Admin2
Fri, 01/23/2026 - 12:44
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ186 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናን ተከታተሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ186 ሺህ በላይ ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና መከታተላቸውን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ሰላሙ አማዶ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ ሥልጠናውን ከተከታተሉት መካከል 145 ሺህ የሚሆኑት በቂ ክህሎት በመጨበጥ የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝተዋል። አጠቃላይ የሥልጠና አፈጻጸሙም 87 በመቶ ደርሷል። ኢንሼቲቩ በዘንድሮው በጀት ዓመት መቶ በመቶ እንዲፈጸም በመንግሥት ግብ የተቀመጠ በመሆኑ፤ በቀሪዎቹ ስድስት ወራት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ሥልጠናው ውጤታማ እንዲሆን በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ክትትል እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል። ከወጣቶችና ስፖርት፣ ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከትምህርት ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንና የሥልጠናው መሳካት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ትልቅ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል። ቀሪዎቹ ሠልጣኞችም በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።