ያሉንን እምቅ አቅሞቻችንን አሟጠን በመጠቀም ክልላችንን የሳይንስ የቴክኖሎጂና ኢኖቨሽን ማዕከል እናደርጋለን ። አቶ ሠላሙ አማዶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳ/ኢ/ቴ/ ቢሮ ሃላፊ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባህል ግንባታ ፤ ዘላቂ ትስስርና የፈጠራ ባለቤቶች መብት ጥበቃ ዙሪያ ለዞንና ልዩ ወረዳ ሃላፊዎችና ቡድን መሪዎች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተካሄደ ይገኛል።
በሥልጠና መድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሠላሙ አማዶ ፣የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስርፀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙሁዲን ሁሴን ፣በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የፓተንት አድሚንስትሬሽን ኤክስፐርት አቶ ሠሎሞን ክዳኔ ፣የዞንና ልዩ ወረዳ ቡደን መሪዎች በተገኙበት ሥልጠናው እየተካሄደ ይገኛል። በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሠላሙ አማዶ እንደገለጹት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማድረግ ለፈጠራ ባለቤቶች ከሚያስገኘው ጠቀሜታ በተጨማሪ የኢኖቨሽን ኢኮስይስተም ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ላይ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል ።
ቴክኖሎጂ ዓለምን በፈጣን ሁኔታ እየቀየረና በራሱም በፈጣን ሁኔታ እየተቀየረ ባለበት ባሁኑ ወቅት የዚህ ፈጣን ለውጥ ፈጻሚዎች የሆንን አካላት አቅማችንን በሥልጠና እየገነባን ብቁና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ ይሆናልም ብለዋል። ክልላችን ለፈጠራ እምቅ ሃይል ያለበት በመሆኑ ተቀናጅተን መሥራት ከቻልን በአገራችን የብልጽግና ጉዞ የድርሻችንን ማበርከት እንችላለንም ያሉት አቶ ሠላሙ በሥልጠናው በሶፍት ዌር ልማት፣በዌብ ሳይት ልማት፣በሥልጠና ማለትም ኢትዮ ኮደርስ በተያያዘ ከንቅናቄ፣ከመረጃ አያያዝ ፣ከሠርተፊኬት ባለቤትነትና ከሥልጠና ውጤታማነት ከመለካት ጋር ያሉ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አያይዘው ገልጸዋል ። የመደመር መንግሥት እሳቤዎች የሆኑትን መፍጠር፣መፍጠን ፣ማብዛትና ማጥራት ሥራዎች በዋናነት የሚፈፀሙት በዚህ መሥሪያ ቤት በመሆናቸው ከቁጥ ቁጥ ሥራ ተላቀን የበዛና ጥራቱን የጠበቀ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በሁለቱ ቀናት የሚሰጠው ሥልጠና ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በሚቀርቡ ሠነዶች ጥልቅ ውይይት በማድረግ ለቀጣይ ሥራ ስንቅ የሚሆን ዕውቀት የሚታገኙበት ይሆናልም ያሉት አቶ ሠላሙ አማዶ ናቸው።
የከምባታ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ጴጥሮስ በበኩላቸው እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው የሥልጠናው አስፈላግነት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው የሥልጠናው ተሣታፊ እንግዶች ከአካባቢው ኀብረተሰብ ጋር የሚትተዋወቁበት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የጎበኙትን ታሪካዊውን የሃምባርቾ ተራራ በመጎብኘት የታሪክ አካል የሚትሆኑበት በእንግዳ ተቀባዩ ዱራሜ ህዝብ ፍቅር የሚትደመሙበት አስደሳች የሥልጠና ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል። ሥልጠናው የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ ዙሪያ ክልሉ አሁን ያለበትን ሁኔታ የሚገመግም ሰነድ የቀረበ ሲሆን ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የፓተንት አድሚናስትሬሽን ከፍተኛ እክስፐርት አቶ ሰለሞን ክዳኔ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ አሰራር እና የፓተንት ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ዝግጅት ላይ የስልጠና ሰነዶች እየቀረቡ ይገኛል።