Skip to main content
zena72

የፈጠራ ባለቤቶችን ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በማስተሳሰር መስራት ለፈጠራ ስራዎችና ሀሳቦች ውጤታማነት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑ ተገለፀ። (ሆሳዕና፣ ጥቅምት 18/2018) ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በፈጠራ ስራዎች ዙሪያ ለመወያየት ያዘጋጀው መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ የፈጠራ ባለቤቶችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን በማስተሳሰር በአጭር ጊዜ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለውን ስራ መስራት የሚያስችል ውይይት ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተግረዋል። በፈጠራ ባለቤቶችና ባለሙያዎች የለሙ ፈጠራዎችና ሀሳቦች ለብሩህ ነጋችን መሰረቶች ናቸው ሲሉም የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል። የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ ባለቤቶችን ሀሳብ ወደ ተግባር የሚቀይሩ የክህሎት ማዕከላት መሆናቸውን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ በተቋማቱ ውስጥ ያሉ መሳሪዎች እና የአሰልጣኞች ዕውቀትና ክህሎት ለፈጠራ ስራዎች ስኬታማነት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል። የፈጠራ ባለቤቶችን ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በማስተሳሰር መስራት ለሀገር ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል። ትስስሩ የፈጠራ ባለቤቶች ሀሳባቸውን በተግባር ለመምከር፣ ለማልማትና ወደ ገበያ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥርም አቶ ሰላሙ ጠቅሰው፣ በሂደቱም የስራ ዕድልና ሀብት እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል ሲሉም አክለው ገልፀዋል። ኮሌጆች የስልጠና ፕሮግራሞቻቸውን ወቅቱ የሚፈልገውን ገበያ መር እንዲያደርጉና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዓላማቸውን ለማሳካት ትስስሩ አጋዥ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮችና የመዋቅር የስራ ኃለፊዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች፣ የፈጠራ ባለቤቶችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተግኝተዋል።