Skip to main content
zena59

የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች አጠቃቀምንና አቅርቦትን በማሳደግ ከወረቀት ነጻ የሆኑ አገልግሎቶችን መስጠት ላይ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸሙን እና የ2018 በጀት አመት ዕቅድን በወራቤ ከተማ ገምግሟል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በዚሁ መድረክ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች አጠቃቀምንና አቅርቦት በማሳደግ ከወረቀት ነጻ የሆኑ አገልግሎቶችን መስጠት ላይ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። በክልሉ ዲጂታል ሊትሬሲ ላይ የአቅም ግንባታ ላይ እና የፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባ የገለጹት አቶ አንተነህ በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሴክተር ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች መቀመርና ማስፋት ይኖርባቸዋል ብለዋል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው ከመድረኩ ብዙ ግብዓት መገኘቱን ገልጸው፤ በክልሉ ተናባቢ ሲስተም ማልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። በ2017 በጀት አመት በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የላቀ አፈጻጸም በክልሉ መመዝገቡን አቶ ሰላሙ ተናግረው በ2018 በጀት አመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ በየደረጃው ቅንጅታዊ አሰራር እና ትብብር መጎልበት ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል። ቢሮው የግብ ስምምነት ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር የተፈራረመ ሲሆን በ2017 በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮቹ ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።