
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 በጀት አመት ከ72,400 በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸው ተገለጸ። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸሙን እና የ2018 በጀት አመት ዕቅድን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በተገኙበት በወራቤ ከተማ እየገመገመ ይገኛል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት በ2017 በጀት አመት ከ49,400 በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ ከ72,400 በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናውን መውሰዳቸው ተናግረዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች አጠቃቀምንና አቅርቦት ከማሳደግ አንጻር በበጀት ዓመቱ 38 ዌብ ሳይቶችን እና 19 ስስተሞችን ማልማትና15 ስስተሞች ከስተማይዝ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል። አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂተላይዝ በማድረግ ብልሹ አሰራርን በመቀነስ ብሎም በማስቀረት የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ መጠነ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። አሁን የቢሮው ምክትል ኃላፊና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስርጸት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሁዲን ሁሴን የቢሮውን የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም ለመድረኩ እያቀረቡ ይገኛል። በሚቀርቡ ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሏል። በመጨረሻም ቢሮው የግብ ስምምነት ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር እንደሚፈረም እና የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የዞንና ልዩ ወረዳ መዋቅሮች ዕውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል። በውይይት መድረኩ የዞንና ልዩ ወረዳ መዋቅሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።