
በዞኑ በ2017 በጀት አመት ቴክኖሎጂ በማልማትና በመጠቀም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የጉራጌ ዞን ሳይንስ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ገለጸ። መምሪያው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምና በ2018 እቅድ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጉራጌ ዞን ሳይንስ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በሰጡት ማብራሪያ በ2017 በጀት አመት ተቋማት ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በካይዘን ፍልስፍና፣ በኔትወርክ ዝርጋታና በሌሎችም በርካታ ስራዎች ተሰርቷል። ከዚህም ባለፈ በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ጥገና በማድረግ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ያነሱት ኃላፊው በዚህም ከመንግስት ይወጣ የነበረው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል። ተቋማት ስራቸውን ቀለል ባለ መልኩ እንዲሰሩ ዲጂታል ሌተሪንግ ሲስተም በማበልጸግ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልጸው የዲጂታል ሌተሪንግ ሲስተም ማህተም፣ የተቋሙ ኃላፊ ፊርማና የመዝገብ ቤት ቁጥርና ሌሎችንም መረጃዎችን የያዘ ወቅቱን የሚመጥን ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል። በዞኑ የፈጠራ ስራዎች ባዛርና ኤግዚብሽን በማዘጋጀት ከ7 መቶ በላይ የፈጠራ ስራዎች እንዲቀርቡ መደረጉን ጠቁመው በዚህም የፈጠራ ባለቤቶች የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንዲተዋወቅ ከመሰራቱን ባለፈ በስፔስ ሳይንስ፣ በሲቪል አቪዬሽን እንዲገቡና ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያሉት። የቴክኖሎጂ ስልጠና በዞኑ በሁሉም ተቋምት የኮምፒውተር አጠቃቀም መነሻ ያደረገ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኮምፒውተር ስልጠና በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተሰርቷል ብለዋል። ከዚህም ባለፈ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸው በስልጠና እንዲያሳልፉ ለማድረግ ከ1 ሺህ 4 መቶ በላይ ተማሪዎች የኮምፒውተር ስልጠና መስጠት መቻሉን ገልጸው በተጨማሪም የኮምፒውተር ጥገና ላይ ስልጠና መስጠቱንም አስረድተዋል። አክለውም ከባለድርሻ አካላት በመቀናጀት የምርምር ስራ በተለይም ከግብርና መምሪያ ጋር በመሆን በዘር፣ በእንሰትና በእንሰሳት በሽታዎች ላይ ውጤታማ ስራ መሰራቱን አውስተው ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ጋር በመሆን የእንሰት መፋቂያ ማሽን የማሰራጨት ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል። እንደ አቶ ደምስ ገለጻ በ2018 በጀት አመት የፈጠራ ባለሙያዎች ስራቸውን የሚሰሩበት የኢኩቤሽን ማዕከል የማቋቋም፣ ዲጂታላይዜሽን ከተቋሙ ባለፈ ሌሎችም ተቋማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል። የሲስተም ማበልጸግና ማልማት፣ የቴክኖሎጂ ስልጠናና ሌሎችም የታቀዱ እቅዶችን በማሳካት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።