Skip to main content
zena54

ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት መቻሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ። የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በትብብር ያለማው ድህረ ገጽ እና እለታዊ የነዳጅ መረጃ መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ ሲስተም የርክክብ መሮሐ ግብር ተካሂዷል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ መሐመድ ኑር ሳሊያ በርክክብ መርሐ ግብሩ እንደገለጹት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት መቻሉን ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን የተደራሽነት አድማስን ለማስፋት ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ ስርዓት አስፈላጊ ስለመሆኑም አማካሪው አብራርተዋል። አሁን ለምቶ ወደ ተግባር የገባው ድህረ ገጽ እና እለታዊ የነዳጅ መረጃ መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ ሲስተም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አማካሪው አስረድተዋል። የተቋሙን የማስፈጸም አቅም ከመጨመር ባለፈ አስፈላጊ መረጃዎችን ለተገልጋዩ ህብረተሰብ አዋጆችን፣ደንቦችን መመሪያዎችን እና ሌሎች ጠቃሚ ሰነዶችን በቀላሉ ማሰራጨት እንደሚያስችልም አቶ መሐመድኑር አስረድተዋል። የነዳጅ መረጃን ከወረቀት ንክኪ ነጻ በማድረግ ዘርፉን ዲጂታላይዝ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረጉን የቢሮ ኃላፊ አማካሪው አብራርተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ም/ ኃላፊ እና የንግድ ስርዓት እና ሸማች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ረሻድ በበኩላቸው በተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። የዲጂታል ሲስተምን መተግበር በተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ወጪ ቆጣቢ እና የጊዜ ብክነትን የሚያስቀር ነው ያሉት ምክትል ኅላፊዋ ግልጸኝነት ያለው አሰራር ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የንግድ ስርዓትን ከማዘመን ባለፈ በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገወጥነት ለመከላከል እንደሚያስችልም ምክትል ኃላፊዋ ተናግረዋል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሀላፊና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንደገለጹት የዲጂታል ሲስተምን መከተል በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገወጥነት መቆጣጠር ያስችላል። የተቋሙን አጠቃላይ መረጃዎች ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ተደረረሽ ለማድረግ ድህረ ገጽ እና እለታዊ የነዳጅ መረጃ መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ ሲስተም አስፈላጊ መሆናቸውንም አቶ ከበደ አብራርተዋል።