
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ለኢኮቴ ከፍተኛ ባለሙያዎች ለአንድ ወር በተለያዩ የሙያ መስኮች ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና በስኬት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ቢሮው ከክልሉ ከተለያዩ አከባቢዎች የተገኙ 118 የኢኮቴ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በወራቤ ከተማ በአራት ዙር በሲስተም ልማትና አስተዳደር፣በአንድሮይድ አፕልኬሽን ልማት፣በሳይበር ሴኩሪቲ፣በኦፊን ማሺን ጥገናና ዕድሳት እና ኣይቲ ኦዶት ዙሪያ ሲያሰለጥን የቆየ ሲሆን በዛሬው እለት 4ኛ ዙሮችን በማስመረቅ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ሰርተፊኬት አበርክቷል። በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቢሮው ምክትልና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ ለኢኮቴ ከፍተኛ ባለሙያዎች በወራቤ ከተማ ለተከታታይ 30 ቀናት በ5 የሙያ መስኮች በአራት ዙር ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በዘርፉ የነበሩ የክህሎት ችግሮችን መቅረፉንና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል። የስልጠናው ዝግጅቱ ብዙ ዋጋ የተከፈለለት መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ ሰልጣኞች የቀሰሙትን እውቀት ወደየአከባቢያቸው ሲመለሱ ወደ ተግባር በመቀየር ራሰቸውንና ማህበረሰቡን ሊጠቅሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሰልጣኞች በስልጠናው አቅማቸውን ከማሳደግም ባለፈ በኦፍስ ማሽን ጥገናና ዕድሳት ስልጠና በተግባር ልምምድ ላይ በወራቤ ሆስፒታል ፣ በስልጤ ዞን ሳኢቴ መምሪያ እና በሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ላይ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ በርካታ የቢሮ ማሽኖች ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረጋቸው ተገልጿል። የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በቴክኖሎጂው ዘርፍ የነበሩባቸውን ክፍተቶች የቀረፈና የቀጣይ ስራቸውን በተቀላጠፈና በውጤታማነት ለማከናወን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።