Skip to main content
zena43

 በዞኑ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች በመደገፍና በማብቃት ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ። በጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ትምህርት መምሪያ በጋራ በመሆን "ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ ሃገር ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው 4ኛ ዙር ዞን አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽንና ውድድር ተጠናቀቀ። የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደ ሀገር ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዞኑ በፈጠራ ስራዎች ያለውን እምቅ አቅም በማጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል። ለዚህም የትምህርት እና የፈጠራ ስራዎች የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን የገለጹት አቶ ላጫ ለዚህም ዘርፉን ሁሉም መደገፍና ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በየአመቱ የሚደረጉ የፈጠራ ስራዎች ውድድር የበለጠ የፈጠራ ስራዎችን እንዲነቃቃና እንዲያድግ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በኢንተርፕራይዞችና በግል እየተሰሩ ያሉ የፈጠራ ስራዎች ይበል የሚያሰኝና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል። እንደ አቶ ላጫ ገለጻ በዘርፉ ውጤታማ ስራ ለመስራት በዞን ደረጃ የኢንኩቤሽን ሴንተር ለማቋቋም እንደሚሰራ ገልጸዋል። በዞኑ እየተሰሩ ያሉ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች በመደገፍና በማብቃት ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ እያንዳንዱ ተቋማት በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የፈጠራ ስራዎች ስርጸት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን በዞኑ እምቅ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸው አንስተው በዚህም በዞኑ በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ለዘርፉ ትኩረት ከመሰጠት ባለፈ የፈጠራ ስራዎች በቅንጅት እየተሰራበት ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ከሌሎችም ተቋማት ጋር መሰል ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል። የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም እንደ ሀገር የሳይንስ፣ የምርምር፣ የፈጠራ ስራዎችና ሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢ ትኩረት በመስጠት የራሱ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ ከላይ እስከ ታች ተግባሩን የሚመራና የሚያግዝ ተቋም በማደራጀት እንደ ሀገር ድጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። በዞኑ ባለፉት አመታት የፈጠራ፣ የምርምርና የቴክኖጂው ስራዎች የሚሳተፉ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወጣቶች፣ ኢንተርፕራይዞች፣ በግል አቅምና ተነሳሽነት ያላቸው ግለሰቦች እና ሌሎችም ለማበረታታትና ለማገዝ ጥረቶች መደረጉና በዚህም አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን አንስተዋል። በዚህም አመቱን በዞኑ ያሉ ትምህርት ቤቶች የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች የሚመሩበት እቅዶች በማስቀመጥና መግባባት ላይ በመድረስ በየትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊውን ውድድርና ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ለፈጠራ ባለቤቶች የተለያዩ ድጋፎች ተደርጓል ብለዋል። የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንዳሉት የውድድሩ አላማ የፈጠራ ስራዎች ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ለአካባቢ ህብረተሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማስቻል ባለፈ የፈጠራ ባለሙያዎችን በሀገር አቅፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። መሰል ውድድሮችና ኤግዚቢሽኖች በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅምና የፈጠራ ስራ ውጤቱ ለህዝቡ እንዲተዋወቅና በስፋት ተግባር ላይ እንዲውል እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት። በዞኑ ያለውን እምቅ አቅም በተገቢው ከመጠቀም ባሻገር ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሸጋገሩ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የኤግዚቢሺኑና የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባዩት የፈጠራ ስራ ውጤቶች መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በሚደረገው የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል። የኤግዚቢሽኑና የውድድሩ አሸናፊዎች በሰጡት አስተያየት ውድድሩ መዘጋጀቱ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለቀጣይ የተሻለ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን አንስተዋል። የተበረከተላቸው ማበረታቻና ሽልማት በቀጣይ ለተሻለና ለላቀ ስራ የሚያነሳሳቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በመጨረሻም በየተቋማቱና በየዘርፉ ከአንደኛ እስከ ሶስት ለወጡ አሸናፊዎች ማበረታቻና እውቅና ተበርክቶላቸዋል።